የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ በትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ጥናት ዙሪያ ስልጠና ሊሰጥ ነው

የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ በትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ላይ ግብዓት ለማሰባሰብ ከመስከረም 14-16/2011 ዓ.ም ስልጠና እንደሚሰጥ አስታወቀ፡፡የዩንቨርስቲው የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ኃይለማርያም ብርቄ  ዛሬ መስከረም 10/2011 ዓ.ም በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደጠቆሙት በሀገር አቀፍ ደረጃ ጥናቱ የተጠናቀቀው የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ግብዓት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለማሰባሰብ ትምህርት ሚንስቴር አቅጣጫ አስቀምቷል ብለዋል፡፡

የስልጠናው ዋነኛ ዓላማ ሁሉም የዩንቨርሲቲው ማህበረሰብ ለውይይት መነሻነት በተዘጋጁት ጽሁፎች ላይ መሰረት በማድረግ በትምህርትና ስልጠና ችግሮቻችን እንዲሁም በመፍትሔ አቅጣጫዎቹ በቀጣይ ለሚዘጋጀው ፍኖተ-ካርታ ግብዓት ለማሰባሰብ ሲሆን በስልጠናውም ከ1800 በላይ መምህራንና አስተዳደር ሰራተኞች በ7 መድረኮች ከ40-42 በሚሆኑ ቡድኖች ተከፋፍሎ ስልጠናው ይሰጣል ብለዋል፡፡

ምክትል ፕሬዚዳንቱ አያይዘው እንደጠቆሙት በዘላቂ ልማት ግቦች፣በ2010 ዓ.ም እቅድ አፈጻጸም ግምገማና በ2011 ዓ.ም እቅዶች ላይ በመወያየት የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ የትምህርት ዘመኑን በውጤታማነት ለመፈጸም ያስችላል ብለዋል፡፡በመጨረሻም ሁሉም የዩንቨርሲቲው ማህበረሰብ በስልጠናው ለይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

 

JoomShaper