የደብረብርሃን ዩንቨርሲቲ ከ 3200 በላይ ተማሪዎችን አስመረቀ

የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ሰኔ 24/2010 ዓ.ም በመደበኛ፣በማታና በተከታታይ መርሃ-ግብሮች በመጀመሪያናበ2ኛ ድግሪ እንዲሁም በከፍተኛ ዲፕሎማ ከ3200 በላይ ተማሪዎችን አስመርቋል፡፡

ዩንቨርሲቲው በ2010 ዓ.ም በመጀመሪያ ድግሪ መደበኛ ፕሮግራም 1586 ወንድ 929 ሴት በድምሩ 2515፣በተከታታይ ትምህርት 295 ወንድ 311 ሴት በድምሩ 606 በአጠቃላይ 1881 ወንድ 1240 ሴት በድምሩ 3121 ተማሪዎችን ሲያስመርቅ፤በድህረምረቃ 2ኛ ድግሪ መደበኛ ፕሮግራም 53 ወንድ 18 ሴት በድምሩ 71፣በተከታታይ ትምህርት 69 ወንድ 8 ሴት በድምሩ 77 ሰልጣኞች አስመርቋል፡፡በአጠቃላይ ዩንቨርሲቲው  በመጀመሪያ ድግሪ 3121፣በ2ኛ ድግሪ 148 በድምሩ 3269 ተማሪዎችን አስመርቋል፡፡

በምረቃው ስነ-ስርዐት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ተፈራ ባሰተላለፉት መልዕክት የዛሬዎቹ ወጣት ምሩቃን አሁን የተፈጠረውን አንጻራዊ ሰላም በማሳጣት ተቻችለውና ተከባብረው ለዘመናት አብረው የኖሩ ህዝቦችን ለመለያየት ብሎም የሃገሪቷን ገጽታ ለማጠልሸት የሚጥሩ ሃይሎችን ነቅተን በመጠበቅ የተያዘው የዲሞክራሲ ለውጥ ጉዞ ወደ ኋላ እንዳይመለስ በመከላከሉ ሂደት አንድ ሆነን ልንታገል ይገባል፡፡የዲሞክራሲና የሰላም ጉዳይ የህልውና ጉዳይ መሆኑን አጥብቆ የሚከተለው መንግስታችን እየተከተለ ያለውን ተስፋ ሰጭ የለውጥ እርምጃ ለማገዝና ለሃገር ልዕልና ለመቆም በዩኒቨርሲቲያችን መልካም አስተዳደር በማረጋገጥ፣የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ፣ ብልሹ አሰራሮችን በመፈተሽና ለለውጥ የሚተጋ ዜጋ በመፍጠር በሚደረገው ሃገራዊ ግንባታ ላይ የበኩላችንን ድርሻ እንድናበረክት በማለት ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የእለቱ የክብር እንግዳና የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የቦርድ ፕ/ር ጽጌ ገብረማርያም በበኩላቸው በቅርቡ በሀገራችን የተጀመረው ለውጥ በሰላማዊ መንገድ እንዲጓዝና ኢትዮጵያችን ሰላም ሰፍኖባት  የዴሞክራሲ ስርዓት አብቦባት ዜጎቿ ሰብዓዊ መብቶቻቸው ተከብሮላቸው መሰረታዊ ፍላጎቶቻቸው ተሟልተውላቸው በደስታ፣በፍቅር፣የሚኖሩባት አገር እንደትሆን ሁላችንም ተግተን እንስራ በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በእለቱ በሴቶችም በወንዶችም አጠቃላይ አሸናፊ ተማሪ እታገኝ ብዙነህ ከእንስሳት ሳይንስ ትምህርት ክፍል 3.98 በማምጣት በወንዶችም በሴቶችም አጠቃላይ አሸናፊ ስትሆን ለዚህ ያበቃት ጊዜዋን በአግባቡ መጠቀም መቻሏ   እንደሆነ ተናግራለች፡፡እንዲሁም ታደሰ ሽፈራው ኮምፒውቲንግ ኮሌጅ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበ ሲሆን ለዚህ ለስኬት ያበቃው የመምህራኖቹና የቤተሰብ ድጋፍ እንደሆነ ተናግሯል፡፡

JoomShaper