ከፍተኛ አመራሩ ለኤች አይ ቪ ኤድስ ትኩረት እንዲሰጥ ጥሪ ቀረበ

 በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ማስተባበሪያ ማዕከል እና በዲኬቲ ኢትዮጵያ የጋራ ትብብር በየዓመቱ ህዳር 22 የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የኤድስ ቀን ‹‹ማህበረሰብ የለውጥ አቅም ነው›› በሚል መሪ ቃል ለ32ኛ ጊዜ ታህሳስ 02/2012 ዓ/ም በልዩልዩ ዝግጅቶች ተከብሯል፡፡

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ሆነ ከከፍተኛ ትምህር ተቋማት ውጪ የሚገኙ ከፍተኛ አመራሮች ለኤች አይ ቪ ኤድስ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩም ጥሪ ቀርቧል፡፡

በበዓሉ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የጥናትና ምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር አልማዝ አፈራ የበዓሉ መከበር ዋናው ሚስጥር በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ በየደረጃው ያሉ አመራር አካላት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው በእቅዳቸው አካታው እንዲሰሩ ለማድረግ ነው ብለዋል፡፡ ሃገራችን ለጀመረችው የለውጥ ጉዞ ዋናው ተዋናይ ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል በመሆኑ በተለይም ተማሪዎች ራሳቸውን ከኤች አይ ቪ ኤድስ በሽታ እንዲጠብቁ በየደረጃው የምትገኙ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት የበኩላቸሁን ድርሻ እንድትወጡ ሲሉም ፕዚዳንቷ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ማስተባበሪያ ማዕከል አስተባባሪ ወ/ሮ አስናቀች ሲሳይ ኤች አይ ቪ ኤድስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንደ ዩኒቨርሲቲ የባህሪ ለውጥ በሚያመጡ ስራዎች  ላይ በማተኮር ስልጠናዎችን የማዘጋጀት፣ ተማሪዎች እየተዝናኑ ቁም ነገር የሚቀስሙባቸውን የመወያያ ፕሮግራሞችን የማመቻቸትና  ጊዚያቸውን በአልባሌ ቦታ እንዳያሳልፉ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በደማቸው ውስጥ ኤች አይ ቪ ቫይረስ ያለባቸውን ተማሪዎች በጥናት የመለየት ስራ መሰራቱን የተናገሩት አስተባባሪዋ  ወጣቱ ራሱን ከኤች አይ ቪ ኤድስ  እንዲከላከል ኮንዶሞችን በማእከሉ በማስቀመጥና የኤች አይ ቪ ኤድስ የደም ምርመራ እንዲያደርጉ ግፊት በማድረግ ራሳቸውን ከኤች አይ ቪ ኤድስ በሽታ እንዲጠብቁ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

የማእከሉ አስተባባሪ አክለውም ዲኬቲ ኢትዮጵና ደብረብርሃን ፋና አዲስ ትውልድ ለተማሪዎች መጽሃፎችን በመለገስ፣በራሪ ወረቀቶችና ብሮሸሮችን በማሰራጨት፣ስልጠናዎችን በመስጠትና አዝናኝ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት ዩኒቨርሲቲውን በማገዝ ላይ መሆናቸውን ገልጸው በቀጣይም በተማረው የባህሪ ለውጥ ላይ በትኩረት እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

በዲኬቲ ኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የስነተዋልዶ ጤና ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ሽመልስ ገበየሁ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚማሩ ተማሪዎች በአብዛኛው እድሜያቸው ከ18  እስከ 24 ዓመት እድሜ ክልል ውስጥ እንደመሆኑ በዓለም አቀፍም ሆነ በሃገር አቀፍ ደረጃ ለኤች አይ ቪ ኤድስ መስፋፋት ሰፊውን ቁጥር የሚይዝ ወጣት ያለበት ነው ብለዋል፡፡ በመሆኑም አመል ወይም የጠባይ ለውጥ በሚያመጡ ፕሮግራሞች (ተከታታይነት ያላቸው የውይይት ፕሮግራሞች)፣ የአቅም ገንባታ ስራ (ህይወትን በእቅድ የመምራት ፕሮግራም) እና በክሊኒኮችና በጤና ተቋማት አካባቢ ኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭትን ለመከላከልና የስነተዋልዶ ጤናን ለመጠበቅ የሚያስችሉ ግብዓቶችን ማሟላት በሚሉ ሶስት ፕሮግራሞች ዙሪያ ዲኬቲ ኢትዮጵያ ከደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ጋር እየሰራ እንደሚገኝም የፕሮጀክቱ አስተባባሪ  ተናግረዋል፡፡ የከፍተኛ ትምህር ተቋማት ኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭትን ለመከላከል በጀት ከመመደብ ጀምሮ የሰው ሀይል በመሟላት ፣የራሳቸው ቢሮ እንዲኖራቸው በማድረግና ግብአቶችን በማሟላት እንዲሁም ከአጋር አካላት ጋር ተባብሮ ለመስራት የሚያሳዩት ፍላጎት አየጨመረ በመምጣት በኩል ከበፊቱ መሻሻል አሳይቷል ያሉት አስተባባሪው ከችግሩ ስፋትና ጥልቀት አንጻር እያንዳንዱን ተማሪ በመረጃ በመድረስ በኩል የሚቀሩ ሰፊ ስራዎች እንዳሉም ነው አክለው የተናገሩት፡፡

በበዓሉ ላይ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ የዩኒቨርሲቲው መምህራን፣  ሰራተኞች እና ተማሪዎች የተገኙ ሲሆን  በአሁኑ ሰዓት የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭት የሚገኝበትን ዓለምአቀፋዊና  ሃገራዊ ሁኔታ የተመለከተ ጥናታዊ ጽሁፍ በዩኒቨርሲቲው ኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ማስተባበሪያ ማእከል አስተባባሪ ወ/ሮ አስናቀች ሲሳይ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡  

 

 

#ማስታወቂያ

ለደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ መምህራንና አስተዳደር ሰራተኞች በሙሉ:

በአሁኑ ስዓት በዩኒቨርስቲያችን የኩፍኝ በሽታ ምልክቶች እየታዩ ስለሆነ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ካሁን በፊት ቢከተቡም ባይከተቡም ክትባቱ በዘመቻ መልክ ይሰጣል፡፡ ስለሆነም የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ መምህራንና አስተዳደር ሰራተኞች ክትባቱን እንድትወስዱ እናሳስባለን፡፡
የኩፍኝ መከላከያ ክትባቱ ህዳር 25-30/2012 ድረስ ለተከታታይ 6 ቀናት ክትባት ይሰጣል፡፡ ስለዚህ ማንኛውም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ክትባቱን በተጠቀሰው ቀንና በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በተዘጋጁ የክትባት ጣቢያዎች እየመጣችሁ እንድትከተቡ እናሳስባለን፡፡

#ማሳሰቢያ፡-ክትባቱ ለነፍሰጡሮች የተከለከለ ነው!!

 

 

 

 

CONTACT US

Communications Affairs Directorate 

Tel: +251116816286

Fax- 0116812065

Po.Box: 445

FPR@dbu.edu.et

Nigus Tadese (PhD)

DBU President

JoomShaper