የኢትዮጵያ የአፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርስቲዎች ኮንሰርቲየም ተመሰረተ::
ጥቅምት 18 ቀን 2017 ዓ/ም፣ በትምህርት ሚኒስቴርና በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት በተልዕኮና የትኩረት መስክ ልየታ መሠረት በአፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲነት የተለዩ፣ የደ/ብርሃን ዩኒቨርስቲን ጨምሮ፣ 15 የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች ባካሄዱት ጉባኤ የአፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲዎች ኮንሰርቲየም ተመስርቷል። በጉባኤው የኮንሰርቲየሙ መመስረቻ ሰነድ ውይይት ተደርጎበት የፀደቀ ሲሆን፣ አምስት አባላት ያሉት የሥራ አስፈጻሚዎች ምርጫም ተካሂዷል። በሥራ አስፈጻሚነት፣ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ፣ የደረብርሃን ዩኒቨርስቲ፣ የወለጋ ዩኒቨርሲቲ፣ የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርስቲ እና የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች ተመርጠዋል። ኮንሰርቲየሙ ዩኒቨርስቲዎች ሀብትን በጋራ ለመጠቀም፣ የጥናትና ምርምር፣ ሥርዓተ ትምህርት ቀረጻ እና የፕሮግራሞች ልማት ሥራዎችን በትብብር ለመስራት የሚያስችላቸው እንደሆነ ተገልጿል:: ከኮንሰርቲየም ምስረታው በተጨማሪ ዩኒቨርስቲዎቹ በአፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርስቲ ሽግግር በተሰሩ ሥራዎች ዙሪያ ልምዳቸውን አካፍለዋል። ሁሉም ዩኒቨርስቲዎች የአፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርስቲ ሽግግር የዝግጅት ማጠናቀቂያና የትግበራ ምዕራፍ ሥራዎችን በመተግበር ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል። በጉባኤው ማጠናቀቂያ ላይ የኮንሰርቲየሙ ዋና ፀሐፊ ሆነው የተመረጡት የደ/ብርሃን ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ንጉስ ታደሰ የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል።