Notice

የሴት መምህራን ተሳትፎ በሁሉም ዘርፍ ሊጎለብት እንደሚገባ ተገለጸ

News

የኢፌዲሪ የባህልና ቱሪዝም ሚንስቴር ዶ/ር ሒሩት ካሳ በጉባኤው ላይ በእንግድነት ተገኝተው የካበተ የመምህርነትና የአመራርነት ልምዳቸውን ለዩኒቨርሲቲው ሴት መምህራን አካፍለዋል፡፡በእለቱ የሴት መምህራን ህብረት ምስረታም ተካሂዷል፡፡

በጉባኤው ላይ ተገኝተው ለእንግዶቹ እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት ንግግር ያደረጉት የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የጥናትና ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር አልማዝ አፈራ እኛ ሴቶች በማህበረሰቡ ከፍተኛ ኃላፊነት የተጣለብን ቢሆንም በተግባር የተሰጠን ቦታ እጅግ ዝቅተኛ ሆኖ ቆይቷል ብለዋል፡፡አሁን ላይ መሻሻሎች እንዳሉ የገለጹት ዶ/ር አልማዝ አፈራ በሁሉም ዘርፍ ከወንዶች እኩል ተወዳዳሪ መሆን የምንችልበት መደላድል ተፈጥሮልናል ነው ያሉት፡፡

ዶ/ር አልማዝ አፈራ በተጨማሪም ከከፍተኛ አመራሩ ጀምሮ በሁሉም የመንግስት ተቋማት 50 በመቶ ሴቶች እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑ የዚህ ማሳያ ነው ብለው ለውጡ ቀጣይነት እንዲኖረውም ህብረት ያስፈልገናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የኢፌዲሪ የባህልና ቱሪዝም ሚንስቴር ዶ/ር ሒሩት ካሳ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገኙ ሴት መምህራን ጥናትና ምርምር የመስራትና የማህበረሰብ አገልግሎት የመስጠት ኃላፊነት እንዳለባቸው ቢያውቁም ከወንዶች እኩል ንቁ ተሳትፎ ሲያደርጉ አይስተዋሉም ነው ያሉት፡፡ሚንስትሯ አክለውም በሴቶች ላይ የሚስተዋለው ችግር የእውቀት ማነስ ሳይሆን ተነሳሽነት የማጣትና ህብረት የመፍጠር ችግር በመሆኑ በወንዶች ላይ የሚታየው የመተጋገዝና የመደጋገፍ ባህል በሴቶች ላይ አይታይም በማለት ተናግረዋል፡፡

የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ሐይማኖት ቢችል በበኩላቸው ውይይቱ የዩኒቨርሲቲው ሴት መምህራን በሚሰሩት ጥናትና ምርምር፣በማህበረሰብ አገልግሎት ተሳትፏቸውና በአመራር ሰጪነት ቦታቸው የበለጠ ውጤታማ የሚሆኑበት፣ ልምድ የሚያገኙበትና ተሳትፏቸውን የሚያጎለብቱበት የማነቃቂያ መድረክ መሆኑን ተናግረዋል፡፡በቀጣይም ተመሳሳይ የውይይት መድረኮችን በመፍጠር አቅማቸውን ለማሳደግ እንደሚሰራም ነው ዳይሬክተሯ የገለጹት፡፡

የውይይቱ የተሳተፉት በዩኒቨርሲቲው የኬሚስትሪ እንዲሁም የስነዜጋና ስነምግባር መምህር  የሆኑት  ወ/ሮ መቅደስ ጌራወርቅና ወ/ሮ መአዛ ተክለአረጋይ የሴት መምህራን ህብረት መመስረቱ ከሚፈጥርላቸው ማህበራዊ ግንኙነት በላቀ በትምህርት ሥራቸው ላይ ለውጥ የሚያመጡበትና እነሱም ተጠቃሚ የሚሆኑበትን እድል እንደሚፈጥርላቸው ተናግረዋል፡፡