Notice

የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የተቀናጀ የግብርና ምርምር ፕሮጀክት ተመረቀ

News

የአሳ፣የዶሮ፣የአትክልትና ፍራፍሬ ላይ ሲያካሂድ የቆየውን የምርምር ፕሮጀክት አጠናቆ ለዞኑ አስተዳደርና ለአካበቢው ማህበረሰብ አስረከበ፡፡

በርክክብ ስነስርዓቱ ወቅት የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ መምህርና መሪ ተመራማሪ ዶ/ር ገዛህኝ ደግፌ እንደተናገሩት ምርምሩ በትንሽ ቦታ አሳን፣ዶሮንና አትክልትን አቀናጅቶ ማልማት የሚያስችል የቴክኖሎጅ እውቀትን በመጠቀም የአሳ፣ የዶሮና የአትክልት ልማቱን አቀናጅቶ መስራት እንደሚቻል ነው ብለዋል፡፡በዚህም የዶሮ ኩሱን ለአሳዎች ምግብ እንዲውል እንዲሁም/Vermy compost/ ቆሻሻን ወደ ጠቃሚ ነገርነትና ማዳበሪያነት የሚቀይሩ ትሎችን ለዶሮዎችና ለአሳ ምግብነት እንዲውል የሚያስችል  እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

አቶ ተፈራ ወንድማገኘሁ የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳደሪ እንዳሉት ይህ ለምርቃት የበቃው የምርምር ስራ የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ በዞናችን ከሚያከናውናቸው ምርምሮች አንዱ ሲሆን በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ፈጻሚነትና በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጅ ሚኒስቴር የገንዘብ ድጋፍ የተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ዋና አስተዳዳሪው አክለው እንዳስታወቁት ይህንን ምርምር በዞናችን በሚገኙ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ለማሰፋት ትልቅ ኃላፊነትና አደራ የተጣለባቸው መሆኑን አውስተው ለተግባራዊነቱም እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጅ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ኢንጅነር ጌታሁን መኩሪያ ባደረጉት ንግግር ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው ከሚደግፋቸው በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች በሚባል ደረጃ ከ60 በላይ  ምርምሮች መካከል የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ አንዱና ውጤታማው በመሆኑ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ በሚችሉ ትናንሽ ፕሮጀክቶች በመደገፍ የሀገራችንን ልማት ማረጋገጥ ይኖርብናል ብለዋል፡፡ይህን ፕሮጀከት የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ለሁሉም ዞኖችና ወረዳዎች እንዲተላለፍ ማኑዋልና ስታንዳርድ ተዘጋጅቷል፡፡የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደርም በአማራ ክልል ለሚገኙ ሁሉም ዞኖች እንዲያደርስ ኃላፊነት የተሰጣቸው ሲሆን በቀጣይ በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲሰራጭ አናደርጋለን ብለዋል፡፡

ዶ/ር አልማዝ አፈራ የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የጥናትና ምርምር ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት በበኩላቸው በዚህ ፕሮጀክት የተሳተፉ ተመራማሪዎችን ያሉትን ተግዳሮቶች ተቋቁመው ለዚህ በመብቃታቸው ምስጋና ቸረዋቸዋል፡፡እንደ ፕሬዚዳንቷ  በሀገራችን እስከ ሁለት ሚሊዮን የሚደርሱ ስራአጥ ወጣቶች መኖራቸው የሚታወቅ በመሆን እንደነዚህ አይነት የምርምር ስራዎች ደግሞ ወጣቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚ በማድረግ ሚናቸው የጎላ ነው ብለዋል፡፡ደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲም ብዙ የምርምር ውጤቶች ያሉት ሲሆን እነዚህን ምርምሮች ወደ ፕሮጀክት መቀየር የሚያስችል ተሞክሮ ስለሆነ ይህ ትልቅ ማሳያ ይሆነናል ብለዋል፡፡በመጨረሻም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጅ ሚኒስቴርንና የኤፍራታና ግድም ወረዳ አስተዳደርን ላደረጉት ድጋፍና ትብብር ምስጋና አቅርበዋል፡፡