Notice

በወቅታዊ ሁኔታ ላይ የተሰጠ የዩኒቨርሲቲው ሴኔት መግለጫ

News

የእሳት ቃጠሎና የድንጋይ ውርወራ የንብረት መውደም ደርሷል፡፡ ይህም ከውጪ ተልዕኮ ተሰጥቷቸው በሚንቀሳቀሱና መማር በማይፈልጉ ጥቂት ተማሪዎች የተነሳ በአብዛኛው ትምህርት ፈላጊና መልካም ስነ-ምግባር ባላቸው ተማሪዎች ላይ የአካል ጉዳት፣ የንብረት መጥፋትና የስነ-ልቦና ጫና ፈጥሮ ቆይቷል፡፡ የደረሰው ጉዳትም የዩኒቨርሲቲውን ሴኔት ያሳዘነው ሲሆን ድርጊቱን አጥብቆ ያወግዛል፡፡

በዚህም መሠረት የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ፣ የዞንና የከተማ እንዲሁም የፌደራል የፀጥታ አካላትና አመራር፣ የሃይማኖት መሪዎች፣የሃገር ሽማግሌዎች፣ የአካባቢው ማህበረሰብና የተማሪ ተወካዮች ባደረጉት ከፍተኛ ርብርብ የሰው ህይወት ሳይጠፋና የከፋ ጉዳት ሳይደርስ ችግሩን ለመፍታት ተችሏል፡፡ ሰላም ለማምጣትና ሁኔታውን ለማረጋጋት ለተሳተፉት አካላት ሁሉ ዩኒቨርሲቲው ላቅ ያለ ምስጋና ያቀርባል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ሴኔት ጥፋተኛ ባላቸው 58 ተማሪዎች ላይ 3 አይነት እርምጃዎች ማለትም በ16ቱ ላይ ከትምህርት እስከ መጨረሻው እንዲታገዱ በ12ቱ ላይ ለ1 አመት ከትምህርትና ሌሎች አገልግሎቶች እንዲታገዱ እንዲሁም በ30 ተማሪዎች ላይ የመጨረሻ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እርምጃ የወሰደ ሆኖ ሳለ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎችና ግለሰቦች ሁሉም ተማሪዎች ከትምህርት የተባረሩ እንደሆኑ ተደርጐ እንዲሁም ምንም እንኳን ሴኔቱ ጥፋትን ብቻ አይቶ የወሰነ ቢሆንም ውሳኔው በአንድ ብሔር ላይ ብቻ የተወሰደ ተደርጐ ሲተላለፍ የነበረው መረጃ የተሳሳተ እና ለሌላ ፖለቲካዊ ፍጆታ ለማዋል የታለመ መሆኑን እየገለጽን በተላለፈው የሴኔት ውሳኔ ቅር የተሰኘ ማንኛውም ተማሪ ካለ ቅሬታውን ደብዳቤ ከደረሰው ቀን ጀምሮ በተከታታይ አምስት ቀናት ውስጥ በአካዳሚክ ምክትል ኘሬዚዳንት ጽ/ቤት በኩል በማቅረብ የሚስተናገድ መሆኑን ሴኔቱ አቅጠጫ አስቀጧል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ሴኔት ሰኔ 05/2011 ዓ.ም ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ የዩኒቨርሲቲው አመራር በየደረጃው ካሉ የተለያዩ አካላት ጋር በመቀናጀት ለ1 ሳምንት ያክል ዘርፈ ብዙ ውይይቶችን በማድረግና በተማሪዎች መካከል እርቀ ሰላም እንዲወርድ የተሰራውን ስራና የደረሰውን ጉዳት በጥልቀት በመገምገም መማር ማስተማሩን ወደ ነበረበት ሁኔታ እንዲመለስ በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ ከዚህ በታች የተመለከቱትን አቅጣጫዎች አስቀምጧል፡፡

  1. በብጥብጡ ወቅት የደረሰውን ጉዳት በዝርዝር በመመልከት ተማሪዎች ወደ ትምህርታቸው እንዲገቡ የሚያስፈልገውን መሠረታዊ ግብአት በተለይም ጉዳት በደረሰባቸው ህንፃዎች ውስጥ ለሚኖሩ ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ የጠፋባቸው ተማሪዎች ተለይተው ማጣቀሻ መጽሐፍት በማይገኝባቸው የትምህርት አይነቶች የማስተማሪያ ጽሁፍ /Hand Out/ በየትምህርት ክፍላቸው ድጋፍ እንዲደረግላቸው፣
  2. አልባሳትና ሌሎች መጠቀሚያዎች የጠፋባቸው ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ተጣርቶ በበጐ አድራጐት ክበብ በኩል አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደረግ፣
  3. በተፈጠረው አለመረጋጋት በተማሪዎች ላይ የደረሰውን የስነ-ልቦና ጫና ለመቅረፍና ለፈተናቸው ዝግጁ እንዲሆኑ በየትምህርት ክፍላቸው አማካኝነት አስፈላጊው ክትትል፣ ምክርና ድጋፍ እንዲደረግላቸው፣
  4. የአካዳሚክ ካላንደሩን በተመለከተ ከሰኔ 6/2011 ዓ.ም ጀምሮ ሁሉም ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው ላይ ተገኝተው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ፣ የተመራቂ ተማሪዎች ማጠቃለያ ፈተና ከሰኔ 13/2011 ዓ.ም ጀምሮ እንዲሰጥ፣ከዚያ ውጪ ላሉ ተማሪዎች ደግሞ ከሰኔ 17/2011 ዓ.ም ጀምሮ የሚሰጥ መሆኑ፣ ክሊራንስ ሰኔ 30 እና ሐምሌ 1/2011 የሰሚሰጥ ሲሆን የምረቃ ጊዜ ሐምሌ 6/2011 ዓ/ም እንዲሆን ተሸሽሎ ተወስኗል፡፡

ፈተናው ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ድረስ የፀጥታ አካላት በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ጥብቅ የሆነ ቁጥጥርና ክትትል የሚያደርጉ ሲሆን ተማሪዎችን ወደ መማሪያ ክፍል እንዳይገቡ በሚከለክሉ፣ በሚያስፈራሩና ጥቃት ለማድረስ በሚሞክሩ አካላት ላይ ህግ የማስከበር ስራው እንዲቀጥል እንዲሁም የደብረብርሃንና አካባቢው ማህበረሰብ እንደ አይኑ ብሌን በሚጠብቀው ዩኒቨርሲቲው ላይ በተቀናጀና በተደራጀ መልኩ ጉዳት ለማድረስ የሚንቀሳቀሱ ሀይሎችን በመምከርና በመጠቆም እንደወትሮው ከዩኒቨርሲቲው ጐን እንዲቆም ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

 
 ሰኔ 5/2011 ዓ.ም

ደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ

ደብረብርሃን፣