Notice

የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የ2012 ዓ.ም የስድስት ወራት እቅድ አፈጻጸምን ገመገመ

News

የስድስት ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርቱን የእቅድና መረጃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደጀኔ ጸጋው አቅርበዋል፡፡ በመሆኑም ሪፖርቱ በዝግጅት ምእራፍ እና በትግበራ ምእራፍ በሚል የቀረበ ሲሆን በዝግጅት ምእራፍ በ2011 ዓ.ም በእሳት የተቃጠሉ ዶርሞች በቂ እድሳት ተደርጎላቸው ተማሪዎችን የመቀበል ስራ ተሰርቷል ተብሏል፡፡በትግበራ ምእራፍ ወቅት ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራው ሰላማዊ ሆኖ እንዲቀጥል ተከታታይ ውይይቶች መደረጋቸው፣ የመሰረተ ልማት አቅርቦትን በተመለከተ አጠቃላይ ግንባታዎች 66 ከመቶ አፈጻጸም ላይ መድረሳቸው፣ 5 ቴክኖሎጂዎች ወደ ህብረተሰቡ መተላለፋቸውን፣ የመደበኛና የካፒታል በጀት አጠቃቀም በግማሽ አመቱ 52.3 ከመቶ መድረሱን ዳይሬክተሩ በሪፖርት ገልጸዋል፡፡

ዳይሬክተሩ አያይዘውም ታቅደው ያልተሰሩ ተግባራት በሚል በዋናነት የዩኒቨርሲቲው መዳረሻ መንገዶች ጫረታ ከወጣ በኋላ በካሳ ክፍያ መጓተት የግምባታ ስራው አለመጀመሩን፣ ግምባታዎች በእቅዳቸው መሰረት ያለመጠናቀቃቸውን፣ የቴክኖሎጂ ካመፓስ ግምባታ የካሳ ክፍያ ዝርዝር ተጠንቶ ያለመቅረቡንና የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ግምባታ ማስፋፊያ ፍቃድ መዘግየት ናቸው ተብሏል፡፡ የተሻሉ አፈጻጸሞች ተብለው ከቀረቡት ውስጥም የመማር ማስተማር ስራው ሰላሙና ጸጥታው የተጠበቀ እንዲሆን መደረጉ፣ የትምህርት ብክነትን የመከላከል ስራ መሰራቱ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትመህርት ቤት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ማእከል መቋቋሙና በመሳሪያ የተደራጀ እንዲሆን መደረጉ እንዲሁም የአንኮበር ፕሮጀክት ምርምር ስራዎች በዋናነት ተጠቅሰዋል፡፡ ባንጻሩ ደግሞ ሜጋ ምርምሮች ያለመጠናቀቃቸውና በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች የሚስተዋሉ ግጭቶች በዩኒቨርሲቲው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ላይ ተጽእኖ ማሳረፍ መቻላቸው ዩኒቨርሲቲውን ያጋጠሙት ፈተናዎች እንደነበሩ አቶ ደጀኔ ጸጋው ባቀረቡት ሪፖርት ጠቁመዋል፡፡

የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የትናትና ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ.ር አበበ ተድላ 300 የምርምር ስራዎች መሰራታቸውን ተናግረው በተወሰኑት የምርምር ስራዎች ላይ የጥራት ችግር እንደተስተዋለ ተናግረዋል፡፡ የበጀት አጠቃቀም ላይ ችግር መኖሩንም ነው ዳይሬክተሩ አክለው የተናገሩት፡፡

የተማሪዎች ስነምግባር ያለበትን ደረጃ በመለየት ውሳኔ ለመስጠት ይረዳ ዘንድ በመምህራን በቅንጅት የተሰራ ጥናት በዶ.ር ጌታው ግርማ እና በዶ.ር ሀይለሚካኤል ለማ ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደረጎበታል፡፡ ጥናቱ የደረሰባቸው ግኝቶችን በግብአትነት መጠቀም አንደሚገባም ነው ተሳታፊዎች የገለጹት፡፡

በተጨማሪም የመምሀራን መገምገሚያ መስፈርት በተመረጡ መምህራን ተዘጋጅቶ በዶ.ር ሽፈራው በቀለ ለውይይት የቀረበ ሲሆን 40፡60 በሚለው መርህ መሰረት 25 ከመቶውን መምህራን በምርምር ስራቸው እንዲገመገሙ፣ 15 ከመቶውን በማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎች በሚያደርጉት ተሳትፎ እና 60 በመቶውን ደግሞ በመደበኛ የመማር ማስተማር ስራቸው በደረጃቸው እንዲመዘኑ በሚል ቀርቦ በውይይት እንዲዳብር ተደርጓል፡፡

በተጨማሪም በስነምግባርና ብልሹ አሰራሮች እንዲሁም በመልካም አስተዳደርና መፍትሄዎቻቸው ዙሪያ የተውጣጡ ቡድኖች ጥናት እንዲያዘጋጁ የተደረገ ሲሆን ጥናቶቹ በአቶ ባዩ ጌታሁን እና  በአቶ ብርሃን አላዩ ለውይይት እንዲቀርቡ ተደርጓል፡፡ የጥናቶቹ አላማም በየደረጃው የሚስተዋሉ ችግሮችን በመለየት ለመፍታት እንደሆነ በአቅራቢዎቹ ተመላክቷል፡፡

የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ.ር ንጉስ ታደሰ ከተሳታፊዎች ለተነሱ አጠቃላይ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ማጠቃለያ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ከካሳ ክፍያ ጋር ተያይዞ ለተነሱ አሰተያየቶቸ ምላሽ ሲሰጡ የግምባታ ስራዎች የዘገዩት የመሬት አዋጁ በድጋሚ በመታየቱ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ጤና ኮሌጅ ግምባታ አካል የሆነው የሃኪም ግዛው ሆስፒታል ሲጠናቀቅ ለሰሜን ሸዋ ሆስፒታሎች ሪፈራል ሆኖ አዲስ አበባ ለከፍተኛ ህክምና የሚሄዱ ታካሚዎችን ማስቀረት በመሆኑ በጥራት ተሰርቶ በቅርብ ጊዜ ይጠናቀቃል ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በተማሪ ስነምግባር ዙሪያ በመምህራን የተዘጋጀው ጥናት የአጠናን ሂደቱን ማድነቅና የበለጠ   በሳይኮሎጂ ዲፓርትመንት ጥናቱ ዳብሮና አድጎ እንዲቀርብ ከተደረገ በኋላ ለሴኔቱና ማኔጅምንት አካሉ ለውሳኔ ሀሳብ ይቀርባል ብለው በተማሪዎቹ የሚንጸባረቁ ችግሮችን ለማስተካከል ዲፓርትመንቶችና ኮሌጆች ራሳችሁን መፈተሸና እያንዳንዱን ተማሪ ማወቅ አለባችሁ ብለዋል፡፡ የተማሪ ስነምግባር ጥሰት በይቅርታ የሚታለፍ አላመሆኑንና የሚወሰዱ የማስተካከያ እርምጃዎችም ከብሄር፣ ከሃይማኖት፣ ወዘተ…ጋር በፍጹም መገናኘት እንደሌለባቸው ፕሬዚዳንቱ ትኩረት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ አያይዘውም የፈጠራ ስራዎችን በማበረታታት በኩል ተማሪዎች ለፈጠራና ትራንስፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርምር ስራዎች የተሻሉ ፕሮጀክቶችን ይዘው ከመጡ የተለየ ትኩረት በመስጠት በበጀት ጭምር መደገፍ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ የተገልጋይ እርካታን አስመልክቶ ለተነሱ ሃሳቦች ምላሽ የሰጡት ፕሬዚዳንቱ ሳይንሳዊ ጥናት ተካሂዶ ካልቀረበ የእርካታ ደረጃ መስጠት አስቸጋሪ ነው ብለዋል፡፡ በመምህራን የተዘጋጀው የመምህራን መገምገሚያ መስፈርት በተመለከትም ከከፍተኛ ትምህርትና ሳይንስና ቴክኖሎጂ የተላከውን መነሻ ሀሳብ በመያዝ የተዘጋጀ በመሆኑ በውይይት በማዳበር የተጠናውን ጥናት ለማሻሻል በሩ ክፍት እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡