Notice

ደ/ብ/ዩ ከሰ/ሸዋ ዞንና ከደ/ብርሃን ከተማ ከተውጣጡ አመራሮች ጋር ውይይት አካሄደ

News

ከደ/ብርሃን ከተማ ከንቲባ ፅ/ቤት፣ ከዞኑና ከከተማው ከተውጣጡ የስራ ሀላፊዎች ጋር ሚያዚያ 23 ቀን 2012 ዓ.ም ውይይት ተካሂዷል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ንጉስ ታደሰ(ዶ/ር) የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ባደረጉበት ወቅት እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው ከተከፈተ ጀምሮ ለከተማውና ለአካባቢው ህብረተሰብ ጉልህ አስተዋፅኦ ያበረከተ መሆኑን ገልጸው ለነዋሪው ሰፊ የስራ እድል የፈጠረ እና የተሻለ የገቢ ምንጭ አምጥቶለታል ብለዋል፡፡ ሆኖም ግን ዩኒቨርሲቲው ከዚህ በላቀ መልኩ መስራት  እንዳለበት አምነው እዛም እዚህም ከሚታዩና ከተበጣጠሱ ተግባራት ወጥተን በህብረተሰቡ ህይወት ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ እንዲመጣ በየደረጃው ከሚገኝ የዞኑ አመራሮች ጋር በቅንጅት ልንሰራ ይገባናል ነው ያሉት፡፡

10 አባላት የያዘ የጥናት ቡድን ተዋቅሮ የህብረተሰቡ ቁልፍ ችግሮች ምንድናቸው? ዩኒቨርሲቲው በምን መልኩ ማገዝ አለበት የሚሉ ጉዳዮችን ይዞ ጥናት አካሂዷል ብለዋል፡፡ የጥናት ቡድኑም በተለያዩ ሙያዎች በርካታ ልምድና እውቀት ያላቸው የዩኒቨርሲቲው ምሁራኖች እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

ዶ/ር አዝመራው አየሁ የጥናት ቡድኑ አካል ሲሆኑ ለውይይት መነሻ የሆነውን የህብረተሰቡ ቁልፍ ችግሮች፣ ያሉ ጸጋዎችና መወሰድ ያለባቸውን የመፍትሔ አቅጣጫዎችን የሚያመላክት ጥናታዊ ጹሑፍ አቅርበዋል፡፡ “ጥቃቅን ጉዳዮች ላይ ጊዜያችንና ሀብታችንን ከማጥፋት ወጥተን ህብረተሰባችን የሚፈልገውንና የጎደለውን ነገር በጥናት ለይተን
ዘለቄታዊ መፍትሔ ልንሰጠው ይገባናል” ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ባለፉት ጊዜያት ያከናወናቸው የጥናትና ምርምር እንዲሁም የማህበረሰብ አገልግሎቶች በሚፈለገው መልኩ ውጤታማ እንዳልነበሩ የጥናት ቡድኑ ገምግሟል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ለዚህም እንደምክንያት የጠቀሷቸው ነጥቦች፡- የተቀናጀ ስራ አለመሰራቱ፣ የአቅም ችግር መኖር፣ በምሁራኑ ዘንድ በቂ የማህበረሰብ አገልግሎት ልምድ አለመኖር፣ ዩኒቨርሲቲው በመማር ማስተማር ስራዎች ላይ ብቻ ማተኮር፣ የሀብት ውስንነት እና ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር ማድረግ እንደሁለተኛ ተግባር መቁጠር ናቸው ብለዋል፡፡ ሌላው ዩኒቨርሲቲው ከዞኑና ከከተማው አመራሮች ጋር በቅንጅት ይሰራሉ ያሏቸውን 7(ሰባት) የትኩረት መስኮችን ጠቅሰዋል፡፡

1ኛ. የዞኑን የተፈጥሮ ሀብት መጠቀም፣ ምርታማነትን መጨመር እና የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ 2ኛ. የትምህርት ጥራቱን በዘላቂነት ማስቀጠል 3ኛ. የኢንቨስትመንት አማራጮችን መለየትና መጠቀም 4ኛ.ተወዳዳሪና ተመራጭ የሰው ሀይል እንዲኖር መስራት 5ኛ.ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶችን መሰነድና ማልማት 6ኛ. ዘመኑን የዋጀውን የቴክኖሎጂ ማላመድና ፈጠራዎችን መስራት 7ኛ. የህብረተሰቡ ጤና እንዲጠበቅ እና  የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኝ መስራት እንዲሁም በእነዚህና በሌሎች በተመረጡ ስራዎች ላይ ሞዴል የሚሆን ስራን ሰርቶ ለሚመለከተው ተቋም የማስተዋወቅና የማስተላለፍ ሂደት ይኖራል ነው ያሉት፡፡

በመቀጠልም ተሳታፊዎቹ በጥናታዊ ጹሑፉ ላይ ያልተዳሰሱ ያሏቸውን ሀሳቦች፣ የፋይናስ ምንጮች፣ የአሰራር ቅደም ተከተልን፣ ስራዎችን መሬት ላይ ለማውረድ የሚገጥሙ የቅንጅት ጉድለቶችን እና የመሳሰሉትን ጥያቄዎችና አስተያየቶችን አንስተዋል፡፡

ጥናታዊ ፅሑፉን ያቀረቡት ዶ/ር አዝመራው እና የደ/ብ/ዩ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ንጉስ ታደሰ በተነሱት ጥያቄዎችና አስተያየቶች ላይ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ዶ/ር ንጉስ ታደሰ እንዳሉት በምሁራኑ ተጠንቶ ለውይይት የቀረበው ጥናታዊ ጹሑፍ ያለቀለትና እንከን የሌለው አድርጎ መወሰድ የለበትም፤ የት ላይ ነው ችግሩ ያለው የሚለውን ለማመላከትና ከተሳታፊው ጠቃሚ ግብዓት ወስዶ ሰነዱን ለማዳበር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ አሁን ላይ ችግሩን በትክክል የመለየት ስራ ተሰርቶ እንዴት ይፈታ? ማን ይፍታው? መቼ? እና ሌሎችንም ጥያቆዎችን ምላሽ ለመስጠት ቀጣይ ጥናት ይካሄዳል ብለዋል፡፡

በመጨረሻም የሰ/ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ገ/ፃዲቅ በበኩላቸው ውይይቱ ችግሮችን በተለያዩ መንገዶች ለማየት የሚያስችል ያለንን እውቀትና ሀብት ቆም ብለን ለመፈተሽ ያግዛል ብለዋል፡፡ በዞኑ ውስጥ ያሉ ችግሮችን፣ የዞኑ ጸጋዎችን እና በቀጣይ መደረግ ያለባቸውን የመፍትሔ እርምጃዎች በጋራ ተነጋግሮና ተግባብቶ ውጤታማ ስራ
ለመስራት መድረኩ የተሻለ አማራጭ ሆኖ እንዳገኙት ተናግረዋል፡፡ “ለእውቀት ልዩ ክብር እንስጥ፤ እውቀት ደግሞ መመዘን ያለበት በውጤትና ችግርን በመፍታት መሆን አለበት” ብለዋል፡፡ በችግሩ ዙሪያ በደንብ ተነጋግረን መፍትሔ ሰጥቶ ውጤት ማምጣት ከተቻለ ዞኑ እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር ሞዴል ይሆናል ነው ያሉት፡፡