Notice

በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የአረንጓዴ አሻራ ቀን መርሀ ግብር በይፋ ተጀመረ

News

በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ዲኖች ዳይሬክተሮችና መላው የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰበ ተገኝተው አይነታቸው የተለያየ ከ1600 በላይ ችግኞችን ተክለዋል፡፡

የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ንጉስ ታደሰ በአረንጓዴ አሻራ ቀን መርሃ-ግብሩ ላይ ባሰሙት ንግግር በ2011 ዓ.ም በተካሄደው የችግኝ ተከላ ፕሮግራም 60 ሺህ ችግኞች ተተክለው 90 በመቶ የሚሆኑት መጽደቃቸውን ነው፡፡ በዘንድሮው የ2012 ዓ.ም ዘመንም በዩኒቨርሲቲው የተፈጥሮ ሀብትና ግብርና ኮሌጅ ከ70 ሺህ በላይ ጽድ፣ሸውሸዌ፣ወይራ፣ዝግባ፣ሰስፓንያ እንዲሁም  ግራቪሊያ ችግኞች ተዘጋጅተዋል ብለዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ አክለውም የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝን በመከላከል ሂደት ጥንቃቄ እያደረግን በአረንጓዴ አሻራ ዘመቻው እንሳተፍ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የዘንድሮውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር እቅድ በመተባባር ማሳካት ይቻላል ሲሉ የተናገሩት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ዴኤታ ዶ/ር ሙሉ ነጋ ከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቻችን ካለፈው ዓመት ጀምሮ በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ዙሪያ በርካታ ስራዎችን ሲሰሩ ቆይተዋል ብለዋል፡፡ ከችግኝ ተከላው ጎን ለጎንም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል እራሱንና ሌላውን ከኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ መጠበቅ እንዳለበትም ነው የተናገሩት፡፡

የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የጥናትና ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር አልማዝ አፈራ በበኩላቸው የደብረብርሃን ከተማ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ባቀረቡት የችግኝ ይቅረብልን ጥያቄ መሰረት የተዘጋጁት ችግኞች እንዲደርሳቸው እንደሚደረግና ለህብረተሰቡ እንደሚከፋፈል አስርደተዋል፡፡

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ ላይ ተሳታፊ የሆኑት የደብረብርሃን የፌደራል ፖሊስ ምድብተኛ ኢንስፕክተር ገብረወልድ ገብረመድህን ከህብረተሰቡ የተገኝን በመሆናችን ስራችን ግዳጅ ብቻ ሳይሆን በልማቱ ተሰታፊ መሆናችንን ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ስነ ጽሁፍ የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ደ/ር ክበበ ጸሀይ በዩኒቨርሲቲው የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ላይ ተሰታፊ ሆኜ 10 ችግኞችን በመትከል አሻራዬን በማሳረፌ እድለኛ ያደርገኛል ብለው የተተከሉት ችግኞች ከፍተኛ እንክብቤ ሊደረግቸላው ይገባል ሲሉም አሳስበዋል፡፡

በእለቱ ከችግኝ ተከላው ጎን ለጎን የደም ልገሳ ፕሮግራም ተካሂዷል፡፡