Notice

ደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ በእንሳሮ ወረዳ ጉዳት ለደረሰባቸው አርሶ አደሮች ድጋፍ አደረገ

News

በድጋፍ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ደረጀ አንዳርጌ እንዳሉት በሰ/ሸዋ ዞን በሚገኙ 2 ወረዳዎች ማለትም በእንሳሮ ወረዳ በሬሳ ቀበሌ እና በአንኮበር ወረዳ ጎረቤላና አልዩአምባ ቀበሌዎች ውስጥ በረዶና ንፋስ ቀላቅሎ በጣለዉ ከፍተኛ ዝናብ ምክንያት በሰዎች አካል ላይ፣ በመኖሪያ ቤቶች፣ በሰብል እና በእንሰሳት ላይ እጅግ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው መረጃው እንደደረሰው ያስከተለውን ውድመትና የጉዳት መጠን የሚያጣራ የባለሙያዎች ስብስብ የያዘ ቡድን አደራጅቶ ቦታው ድረስ በመላክ እንዲያጠኑት ተደርጓል፡፡ የጥናት ቡድኑ ባጠናውና ባቀረበው ምክረ ሃሳብ መሰረት የዩኒቨርሲቲው የማኔጅመንት አካል በጥልቀት ተወያይቶ አፋጣኝ ውሳኔ ሰጥቶበታል ብለዋል፡፡

በዚህም መሰረት የደረሰውን የጉዳት መጠን ታሳቢ በማድረግ በሁለቱም ወረዳዎች ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የ2 ሚሊዮን ብር አፋጣኝ እርዳታ ለመስጠት እንደተወሰነ ገልጸዋል፡፡ በዛሬው እለትም እንሳሮ ወረዳ በሬሳ ቀበሌ ጉዳት ለደረሰባቸው አርሶአደሮች ከ1 ሚልዮን ብር በላይ ግምት ያለው ለቤት መስሪያ የሚሆን 5ሺህ ቆርቆሮ ለመጀመሪያ
ዙር ድጋፍ ተደርጓል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አክለውም በቀጣይ አርሶ አደሮቹን በዘላቂነት ተቋቁመው ወደ ቀደመ ህይወታቸው እንዲመለሱ ዩኒቨርሲቲው የተቻለውን ነገር ሁሉ ያደርጋል ብለዋል፡፡

የእንሳሮ ወረዳ ዋና አፈ-ጉባኤ አቶ አበራ ባዩ እንደገለጹት በእንሳሮ ወረዳ በሬሳ ቀበሌ ነሃሴ 19 ቀን 2012 ዓ.ም በረዶ ቀላቅሎ በጣለው ዝናብ ምክንያት በመኖሪያ ቤቶች፣ በሰብል እና በእንሰሳት ላይ እጅግ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰ ተናግረዋል፡፡ ከ30-50 ደቂቃ በቆየው በአይነቱና በመጠኑ ለየት ያለ በረዶ ቀላቅሎ በጣለው ዝናብ ምክንያት በ1344 ሄክታር መሬት ላይ የተዘራ የማሽላ፣ ጤፍ፣ በቆሎ እና ሰሊጥ ሰብሎች ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን ገልጸዋል፡፡ እንደ አፈጉባኤው ገለፃ ከ3040 በላይ አርሶአደሮች ተፈናቅለው በአሁኑ ሰዓት በድንኳንና በዳስ ውስጥ ይገኛሉ ነው ያሉት፡፡ አርሶአደሮቹ በቀጣይ ልጆቻቸውንና ቤተሰቦቻቸውን የሚመገቡት በቂ ምግብ እንደማይኖራቸው ገልጸው የሚመለከታቸው መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ባለሀብቶች፣ የአካባቢው ተወላጆችና በሀገር ውስጥና በውጪ ያሉ ወገኖች የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ያደረገውን በጎ ምግባር ተከትለው በከፋ ችግር ላይ ለሚገኙት አርሶአደሮች የምግብ፣ የአልባሳትና ሌሎች ቁሳቁሶችን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዋና አፈ-ጉባኤው አክለውም እንደ ሀገር የኮሮና ወረርሽኝ በእጅጉ በተስፋፋበትም ወቅት ዩኒቨርሲቲው ለወረዳው የንጽህና መጠበቂያ ሳኒታይዘርና ሌሎች ቁሳቁሶችንም ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

ከ1 ሚልዮን ብር በላይ ግምት ያለው ለቤት መስሪያ የሚሆን 5ሺህ የቆርቆሮ ድጋፍን ከአርሶአደሮቹ የተወከሉ የአካባቢው ሽማግሌዎች፣ የቀበሌው አስተዳዳሪ፣ የወረዳው ዋና አፈ-ጉባኤ እና ከደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የተወከሉ አመራሮቻና የጥናት ቡድን ተወካዮች በተገኙበት በእንሳሮ ወረዳ ለሚ ከተማ ርክክብ እንደተደረገ ለማየት ተችሏል፡፡

የበሬሳ ቀበሌ ዋና አስተዳዳሪና የጉዳቱ ሰለባ አርሶአደር የሆኑት አቶ አምባው ሰልፈኛ በበኩላቸው ደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ በተጠየቀው የእርዳታ ጥሪ መሰረት የባለሙያዎች የጥናት ቡድን አደራጅቶ ቀበሌው ድረስ በመላክ በአርሶአደሩ መኖሪያ ቤት፣ በእንሰሳትና ሰብልሎች ላይ የደረሰውን ጉዳት ተመልክቶ አፋጣኝ እርዳታ በማድረጉ ዩኒቨርሲቲው ከህብረተሰቡ ጎን መሆኑን አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡ ቀደም ሲል ዩኒቨርሲቲው የተሻሻሉ የማሽላና የጤፍ ዝርያዎችን በማምጣት ለአርሶአደሩ ሲሰጥ እንደነበርና ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል፡፡  አቶ አምባው ሰልፈኛ ለተደረገላቸው ድጋፍ በቀበሌቸው ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡