የፌደራል ከፍተኛ አመራሮች፣ የዞን አመራሮች፣የሀይማኖት ተቋማት ተወካዮች፣የኢንዱስትሪ ባለቤቶችና ማናጀሮች፣ የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የቦርድ አባላት፣ በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት ተቋማት አመራሮች፣ የዩኒቨርሲቲው መምህራን ሰራተኞችና ተማሪዎች ተገኝተውበታል፡፡
የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ንጉስ ታደሰ በእንኳን ደህና መጣችሁና በመክፈቻ ንግግራቸው በዩኒቨርሲቲው የኢንዱስትሪ ትስስር ዙሪያ ጅምር ስራዎች መኖራቸውን የገለፁ ሲሆን እስካሁን የተሰራው ስራ አመርቂ አለመሆኑንም ጠቁመዋል፡፡መንግስት ለተቋማት ትስስር ትኩረት በመስጠት ቀድሞ የነበረውን የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስር በአሁኑ ጊዜ ሌሎችንም ተቋማት አካታች ባደረገ መልኩ የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ፣ የምርምር ተቋማትና ኢንዱስሪ ትስስር በሚል የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኮሌጆችንና የምርምር ተቋማትን የሚያካትት ሆኖ ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ አክለውም በአካባቢው የሚገኙ የኢንዱስትሪዎች ብዛት ብቻውን ግብ ስለማይሆን እያንዳንዱ ተቋም በትብብር ለመስራት በሩን ክፍት ማድረግ አለበት በማለት ተናግረዋል፡፡ እንዲሁም ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በቀጣይ አንዲሰራባቸው በተመረጡ የትኩረት አቅጣጫዎች ማለትም በኢንጅነሪግ ፣በጤና፤በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ እና በግብርናው ዘርፍ አመርቂ ስራዎችን በመስራት በዙሪያው ለሚገኙ ኢንዱስትሪዎች የሰለጠነ የሰው ሀይልማፍራት የአካባቢውን ህብረተሰብ የመልማት ችግር የሚቀርፍ ጥናትና ምርምር በስፋትና በጥራት ለመስራት የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል ፡፡ ከቀረቡት ፕሮጀክቶች ውስጥ አንዱ ደብረ ብርሃን ከተማ የምታሳየውን ፈጣን እድገት የሚመጥን የተቀናጀ መዋቅራዊ ፕላን ለመስራት የተዘጋጀው እቅድ ይገኝበታል በማለት ገልጸዋል፡፡ይህ እቅድ ከተማዋ ለሚቀጥሉት ሰላሳ ዓመታት የምታደርገውን እድገት ታሳቢ በማድረግ የተዘጋጀ ሲሆን በሰሜን ሸዋ ዞን ያለውን የኢንቨስትመንት አቅም ለይቶ በመሰነድ ባለሃብቶች ሊሰማሩ የሚችሉባቸውን እና ዘለቄታዊ የሆነ ሀብት ማፍራት የሚችሉባቸውን የኢንቨስትመንት አይነቶች ለመለየት ታስቦ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
ክቡር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ባደረጉት ቁልፍ ንግግር ዩኒቨርሲቲዎች እውቀታቸውን ለአካባቢው ማህበረሰብ በማዋል የህብረተሰቡን የኑሮ እድገት ማፋጠን አለባቸው ብለዋል፡፡ አዳዲስ ምርምሮችን በማድረግም ከከተማዋ የእድገት ፍጥነት ጋር እኩል የሚራመድና በአካባቢው ለልማት የሚደረገውን ጥረት በማገዝና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ትስስር መፍጠር ይገባል ሲሉ አክለዋል፡የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የልማቶች ሁሉ አውራ የሆነውን ትውልድን የመቅረፅ ስራ ከመስራቱ በዘለለ በአካባቢው የሚደረገውን ልማት ለማገዝ የደብረ ብረሃን ከተማን ሮድ ማፕ አዘጋጅቶ ወደ ትግበራ እንዲገባ ትልቅ ስራ በመስራቱ ሊመሰገን ይገባል በማለት ክቡር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ተናግረዋል፡፡ዩኒቨርሲቲው በዚህ ጥረቱ ወደፊት ብዙ ልምድ የሚቀሰምበት፣የሀገራችን ትልቅና ሞዴል ዩኒቨርሲቲ እንደሚሆን አልጠራጠርም ብለዋል፡፡
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ“ ትስስር በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ፖሊሲና ስትራቴጅ” በሚል ርዕስ- ባቀረቡት ጽሁፍ ቁልፍ የትስስር ፖሊሲ መሰረታዊ ጉዳዮችን አንስተው የኢንዱስትሪዎችና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በአተገባበር ሂደት ትስስራቸው ላይ ስጋት አለ ሲሉም ተናግረዋል፡፡ስጋቱን ለመቅረፍም የኢንዱስትሪዎችን ትስስር ማጠናከር ይገባል ነው ያሉት፡፡
ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የሰሜን ሸዋ አካባቢ የልማት ኮሪደር ለማፋጠን፤ ከኢንዱስትሪዎች ጋር ትስስርን ለማጠናከር፤ የማህበረሰብ ችግር ለመፈታትና ከአጋር አካላት ጋር በመሆን የትኩረት አቅጣጫዎችን በመለየት ተመራማሪዎች በሚያከናውኑት ጥናት መሰረት የትግበራ ስልት በመንደፍ ወደ ስራ እየተገባ መሆኑን ዶ/ር አዝመራው አየሁ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የጥናትና ምርምር ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ገልጸዋል፡፡
በእለቱም ”የተቋማዊ ትስስር ልምድ ልውውጥ ” በፕ/ር ዳንኤል ቅጣው፣ “በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የሚሰሩ ፕሮጀክቶች የዳሰሳ ጥናት” በዶ/ር አዝመራው አየሁ”የደብረብርሃን ከተማ መዋቅራዊ ፕላን” በዶ/ር ጌታመሳይ፣ ” ሞደል የመንደር ፕሮጀክት፤ በዶ/ር አውራሪስ ሀይሉ፣ “የሰሜን ሽዋ ዞን የኢንቨስትመንት አቅም” በዶ/ር ፈለቀ ባዩ፣ “የታሪክ፣ የባህል ቅርስ ጥበቃ ለዘላቂ ቱሪዝም ልማት” በዶ/ር ዘመነወርቅ ዮሃንስ፣ “ዘላቂ የስራ ፈጠራና የክህሎት እድገት” በሰለሞን እስጢፋኖስ በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች በተከታታይ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን ከተሳታፊዎች በተነሱት ሀሳቦችና ጥያቄዎች በክቡር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደህንነት ልዩ አማካሪ ፣ በአቶ መላኩ አለበል የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚንስትር እና በዶ/ር ንጉስ ታደሰ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት የማብራሪያና የማጠቃለያ ሃሳቦች ተሰጥቶባቸዋል፡፡ በመጨረሻም በምኒሊክ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ግንባታ የማስፋፊያ ስራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት የእውቅናና የምስጋና የምስክር ወረቀት ተስጥቷል፡፡