Notice

ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሀ ግብር አካሄደ

News

የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ንጉስ ታደሰ (ዶ/ር) እንዳሉት በዩኒቨርሲቲያችን የተዘጋጀው የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሀ ግብር ለየት የሚያደርገው የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስተር ባዘጋጀው አጠቃላይ ዓመታዊ የስራ አፈጻጸም ምዘና ከአፕላይድ ዩኒቨርሲቲዎች ተወዳድሮ አንደኛ ደረጃን በማግኘቱና የኢቲዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ሙሌት በስኬት በመጠናቀቁ ነው ብለዋል፡፡ ባገኘነው ድል ላይ ሆነን ተጨማሪ ድል ለማስመዝገብ ጠንክረን የምንሰራበት ጊዜ ነውም ሲሉ አክለዋል፡፡

በ2011 እና በ2012 ዓ/ም በዞኑ በሚገኙ የደብረ ብርሃን ከተማ፣ አንጎለላና  ጠራ፣ ሞጃና ወደራ ወረዳዎች የተለያዩ ሀገር በቀል ችግኞችን ለማህበረሰቡ በማሰራጨትና በመትከል የበኩሉን አስተዋጽኦ ያበረከተው ዩኒቨርሲቲያችን በዚህ ዓመትም ለአካባቢው የሚጠቅሙ በምርምር የተሞከሩና የአካባቢውን የአየር ጸባይ ተቋቁመው ውጤታማ መሆን የሚችሉ ከ1 መቶ 50 ሺህ በላይ ሀገር በቀል ችግኞችን በራሳችን በማዘጋጀት ለአካባቢው ማህበረሰብ እየተከፋፈለ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ችግኝ መትከል ልጅን ተንከባክቦና ኮትኩቶ ለሃገር እንዲጠቅም አድርጎ እንደማሳደግ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ ለኣካባቢ፣ ለሃገርና ለአለም ማህበረሰብ ትልቅ ትርጉም አለው ሉት ፕሬዚዳንቱ ችግኝ መትከል አካባቢን የማስዋብ፣ አየር ንብረትን የመጠበቅና ንጹህ አየር የማግኘት ጉዳይ እንደሆነም ነው የገለጹት፡፡

ፕሬዚዳንቱ አክለውም ከአጎራባች ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በጋራ በወንድማማችነት መንፈስ ችግኝ ስንተክል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንደ አሁኑ በጋራ ለሀገርና ለማህበረሰቡ  የሚተርፉ ስራዎችን እንድንሰራና አቅም የመፍጠር ባህላችንም እያጎለበተ እንዲሄድ ስለሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡ በቀጣይም ከኮተቤ ምትሮፖሊታንትና ሰላሌ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ለሚኖረን የሁለትዮሽ ጥምረት መሰረት የምንጥልበት እለት ነውም ብለዋል፡፡

በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ የግብርናና ተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ ዲንና የልኡካን ቡድኑ አስተባባሪ ወ/ሮ የሸዋድንበር መኮንን ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲና ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ የጋራ ከሚያደርጓቸው ጉዳዮች አንዱ የጋራ ተጠቃሚ ወረዳዎች ያሏቸው መሆኑና በጋራ ለማልማትም ምቹ እድል መኖራቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ሁለቱም ዩኒቨርሲቲዎች በአባይ የላይኛው ተፋሰስ ቦታዎች ውስጥ የሚገኙ እንደመሆናቸውም የአባይ ወንዝ በደለል እንዳይሞላ የልማት ስራዎችን በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸው ነባራዊ ሁኔታዎች አሉ ሲሉም ነው የገለጹት፡፡

ወ/ሮ የሽዋድንበር መኮንን አክለውም ዛሬ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ያዘጋጀው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሀ ግብር በጥናትና ምርምር ማህበረሰብ አገልግሎት ቀጣይ ስራዎችን በጋራ እንድንሰራ መሰረት የጣለ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በኮተቤ ሜትሮፖሊታንት ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ደሞወዝ አድማሱ (ዶ/ር) ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በተከታታይ ጊዜያት ቀዳሚ ደረጃን በመያዝ ትልቅ ተስፋን ያነገበና ለሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችም አርአያ የሆነ ዩኒቨርሲቲ እየሆነ መምጣቱን ጠቁመው ከመማር ማስተማር ስራው በዘለለ የአረንጓዴ አሻራ የማስቀመጥ ሌጋሲ አዘጋጅቶ አጎራባች ዩኒቨርሲቲዎችን ሲጠራ ልማቱም ጥፋቱም የጋራችን እንደሆነ በማሰብ ነው ብለዋል፡፡ በአንድ አካል ብቻ የሚሰራ ስራ ሙሉ አይደለም ያሉት የኮተቤ ሜትሮፖሊታንት ዩኒቨርሲቲ ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደምወዝ አድማሱ ዛሬ የጀመርነውን በጋራ የመስራት ባህል ሌሎችም ተቋማት የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲን ምሳሌ መከተል እንዳለባቸው ተቁመዋል፡፡

በፌደራል የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስተር የአይሲቲ ዘርፍ ዳይሬክተር ጀነራል ደ/ር ኢንጅነር አብዮት ሲናሞ በበኩላቸው የዛሬው መርሀ ግብር ሀገራችን የጀመረችውን የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የሚያስቀጥልና የዚሁ አካል መሆኑን ገልጸው ዩኒቨርሲቲዎች በቅንጅት ህብረትና አንድነትን ፈጥረው አሻራቸውን የሚያኖሩበት በአይነቱ የተለየ መርሀ ግብር ነው ብለዋል፡፡

በአረንጓዴ አሻራ ስራችን ተስማሚ የአየር ጸባይ በማምጣትና ዝናብን በማሻሻል ረገድ ውጤቶች እየታዩ በመምጣታቸው የአፈር መሸርሸርን ለማስቀረት፣ ውሃን በመቋጠር ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ጠቀሜታው የጎላ ስለሆነ ማህበረሰቡና ሌሎች ተቋማትም ሊማሩበት የሚገባ አርአያነት ያለው ተግብር እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

ዳይሬክተሩ አክለውም በዚህ ዘርፍ የኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚንስቴር እንደ ሀገር የችግኝ ተከላ ሂደቱንና  ከተከላ በኋላ የሚኖሩ ድጋፎችን በቴክኖሎጂ የታገዘ ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡