Notice

የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በጤና ሳይንስ ኮሌጅ በመጀመሪያና በሁለተኛ ድግሪ ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች አስመረቀ

News

 የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የአስራት ወልደየስ ጤና ሳይንስ ካምፓስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ቴዎድሮስ ክፍለዮሀንስ  ባደረጉት ንግግር ሀገራችን ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የጤና ባለሙያ እጥረት ካለባቸው አገሮች አንዷ መሆኗን ተናግረው የጤና ባለሙያዎችን  ቁጥር ከፍ ለማድረግም ቀን ከሌሊት እየሰራች ትገኛለች ብለዋል፡፡

አያይዘውም ሀገራችን ኢትዮጵያ በአሁን ሰዓት ባጋጠማት የህልውና አደጋ ዘመቻ በርካታ ወገኖቻችን የእናንተን ድጋፍና እርዳታ በሚሹበት ወቅት በመመረቃችሁ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባችሁ አውቃችሁ ተመርቃችሁ ወጥታችሁ በጥሩ ስነ ምግባር የታነጻችሁ ሆናችሁ በሙያችሁ የወገናችሁን ስቃይ የምታስታግሱ እንድትሆኑ አደራ እላለሁ ሲሉም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ዋና ስራ አስፈጻሚው  እንደተናገሩት  የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በአስራት ወልደየስ የጤና ሳይንስ ካምፓስ በህክምናና በጤና ሳይንስ ዘርፍ ዘመኑ በደረሰበት ቴክኖሎጂ የታገዘ ስልጠና ለመስጠት ዝግጅቱን አጠናቋል ብለዋል፡፡

በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ገስጥ ጥላሁን ባደረጉት ቁልፍ ንግግር ሃገራችን ኢትዮጵያ ያጋጠሟትን  እንቅፋቶች በከፍተኛ ትእግስት አልፋችሁ ለዚህ ምረቃ በመብቃታችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡ ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ህይወት ልትታደጉ ስለበቃችሁም ትልቅ ኩራት ሊሰማችሁ ይገባል ብለው ሃገራችን አሁን ላይ ካጋጠሟት የሰላም እጦት የተነሳ ድርብ ሃላፊነት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

ኃላፊው በንግግራቸው የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የጤናውን ዘርፍ ለማሳደግ የሚያስችሉ የእውቀት፣ የክህሎትና የተግባቦት ስልጠናዎችን እየሰጠ  አቅም ያለው የሰለጠነ የሰው ሃይል የማፍራት ተልእኮውን እየተወጣ እንደሚገም ገልጸዋል፡፡

በእለቱ የስራ መመሪያ የሰጡት የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ግርማ የሽጥላ እንዳሉት ህብረተሰቡ፣ቤተሰባችሁና ዩኒቨርሲቲው ለዛሬዋ ቀን ሲያበቋችሁ የስራ ታታሪነትን፣ስነ-ምግባርንና የስራ ችሎታን በማጎናጸፍ ሲሆን ከዚህ በኋላም ራሳችሁን በማያቋርጥ የማብቃት ኃላፊነት ውስጥ አድርጋችሁ ሀገራችሁንና ህዝባችሁን እንድታገለግሉ በማለት የስራ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡