ሰኔ 27/2016 ዓ.ም፡፡ ደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ በቅድመ ምርቃና ድህረ- ምርቃ ፕሮግራሞች በጤና፣ በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ፣ በህግና በኢንጂነሪንግ የትምህርት ዘርፎች በመደበኛው፣ በማታውና በተከታታይ ፕሮግራሞች በመጀመሪያ ዲግሪ 882ና በሁለተኛ ዲግሪ 366 በአጠቃላይ 1248 ተማሪዎችን ለ16ኛ ጊዜ በዛሬው እለት አስመረቋል፡፡ ከነዚህ ተመራቂ ተማሪዎች መካከል 36% ያህሉ ሴቶች መሆናቸውም ታውቋል፡፡
በምርቃት ስነ- ስርዓቱ ላይ በኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የአይሲቲና ዲጂታላይዜሽን ዘርፍ ሚኒስቴር ዲኤታ ይሽሩን አለማየሁ (ዶ/ር)፣ የዩኒቨርሲቲው ካውንስል አባላት፣ የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ መምህራንና ሰራተኞች፣ ተመራቂ ተማሪዎችና
የተመራቂ ቤተሰቦች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና የሚዲያ አካላት ተግኝተዋል፡፡
በምርቃት ፕሮግራሙ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ንጉስ ታደሰ (ዶ/ር) እንደገለጹት ደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ2022 ዓ.ም በሃገሪቷ ካሉ የተግባር ዩኒቨርሲቲዎች በተግባር ተኮር ትምህርትና ምርምር ግንባር ቀደም ዩኒቨርሲቲ ለመሆን ራዕይ አስቀምጦ እየሰራ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አክለውም በ2016 ዓ.ም ለመውጫ ፈተና ከተቀመጡት መደበኛ ተማሪዎች ውስጥ 90.8% በማሳለፍ ከግንባር ቀደም ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ለመሆን ችሏል ብለዋል፡፡ በመማር ማስተማር፣ በጥናትና ምርምር እንዲሁም በማህበረሰብ ጉድኝት ስራ የራሱ የሆኑ ተልዕኮዎችን፣ ራዕይና እሴቶችን ቀርጾ ለተግባራዊነታቸው እየሰራ የሚገኘው ደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የሀኪም ግዛው መታሰቢያ ሆስፒታል ደግሞ ከግንቦት 1/2014 ዓ.ም ጀምሮ በዘመዊ ቴክኖሎጂዎች የታገዘ ህክምና እየሰጠና ከዚህ ቀደም ማህበረሰቡ ሲጉላላባቸው የነበሩ የሲቲ ስካንን ህክምና ጨምሮ ለአካባቢው ማህበረሰብ የሚበጅ ትልቅ ስራ እየሰራ እንደሆነ ገልፀው በተጨማሪም የደብረብርሃን ሪጅዮ ፖሊታን ከተማ መዋቅራዊ ፕላን በመስራት በቅርቡ ለከተማ መስተዳደሩ እንደሚያስረክቡም ተናግረዋል፡፡
የምረቃ ስነ-ስርዓቱ የስራ መመሪያ ንግግር ያደረጉት በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የአይሲቲና ዲጂታላይዜሽን ዘርፍ ዲኤታ ይሽሩን አለማየሁ (ዶ/ር) እንዳሉት የየኒቨርሲቲዎች ዓላማ ብቃት ያለው የሰው ሀይል በሚፈለገው ብዛትና ጥራት ማፍራት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡በአይሲቲና ዲጂታላይዜሽን ዘርፍ ውጤታማ የሆኑ ሀገራት መሰረታቸው የትምህርትና ስልጠና ስርዓታቸው ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽንን በተለይም በአሁኑ ስዓት የዲጅታል ኢኮኖሚ በሚገነባበት በዚህ ስዓት የሰው ኃይል አቅማቸውን ማሳደግ በመቻላቸው ነው ብለዋል፡፡ አክለውም ዩኒቨርሲቲዎቻችን በተሰጣቸው ሀገራዊ ተልዕኮ መሰረት ትውልዱን በአዲሱ የዓለም ስርዓት ውስጥ ውጤታማ እንዲሆኑ መጨውን ጊዜ መሰረት የሰው ሀብት የሚፈራባቸው፣ አዳዲስ ሀሳቦች የሚፈልቅባቸው፣ ባህላዊ እሴቶች የሚጎለብቱበት፣ እውቀት ወደ ተግባር የሚለወጥበት፣ የመተሳሰብ፣ የመቻቻልና የአብሮነት ባህል የሚቀመሩበት ማዕከላት አድርጎ መስራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡
አክለውም ተመራቂዎችም በዚህ ሂደት ውስጥ አልፋችሁ በዩኒቨርሲተ ቆይታችሁ ያገኛችሁትን ስንቅ ሰንቃችሁ ለዚህ ምረቃ እንደበቃችሁ ተስፋ አደርጋለሁ ብለው የዛሬው ምርቃታችሁ ወደ አዲስ ምዕራፍ የምትሸጋገሩበት እንጂ የመጨረሻ አለመሆኑን ተረድታችሁ በዩኒቨርሲቲው የቀሰማችሁትን እውቀትና ክህሎት በመያዝ ወደ ማህበረሰቡ ስትቀላቀሉ የምታገኙትን መልካም እሴት በመጠቀም ራሳችሁንና ሀገራችሁን በማገልገል በሀገር ግንባታ ላይ የበኩላችሁን አሻራ እንድታሳርፉ ሲሉ አሳስበዋል፡፡
በመደበኛ ትምህርት ፕሮግራም ከሴቶች አጠቃላይ 3.93 በማምጣት ተመራቂ ራዕይ ግርማ ከፋርማሲ ትምህርት ክፍል የዋንጫ ተሸላሚ ስትሆን 3.95 ብልጫ ነጥብ በማምጣት ደግሞ ከዚሁ ትምህርት ክፍል ተመራቂ ተገኘ ተስፋዬ ዘሪሁን የ2016 ዓ.ም አጠቃላይ የዋንጫና ሜዳለያ ተሸላሚ ሆኗል፡፡
እንዲሁም ተመራቂ ቤተልሄም ሰለሞን ከምህንድስና ኮሌጅ ዳዊት ሻውል ከህግ ት/ቤትና በላይ ብርሃኑ ከኮምፒውቲንግ ኮሌጅ የሜዳለያ ተሸላሚዎች ሆነዋል፡፡