Notice

በዩኒቨርሲቲው ተከስቶ የነበረው የጸጥታ መደፍረስ ወደ ነበረበት ለመመለስ የተካሄደው ውይይት በስኬት ተጠናቀቀ

News

የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ መምህራን የአስተዳደር ሰራተኞችና የተማሪ ተወካዮች በተገኙበት ሰፊ ውይይት በማካሄድ ሰኔ 4 ቀን 2011 ዓ.ም በስምምነት ተጠናቀቀ፡፡

በውይይቱ ከተማሪዎች የተነሱ ዋና ዋና ጥያቄዎች 1. ሰላማችንና ደህንነታችን ይጠበቅ፣ ዋስትና ይሰጠን 2. የጠፉ ንብረቶች፣ አልባሳት፣ የትምህርት መማሪያ መፍትሄ ይሰጠን 3. ለተጎዱ ተማሪዎች እንክብካቤ ይደረግ 4. የተባረሩ ተማሪዎች ውሳኔው እንደገና ይታይልን 5. የዩኒቨርሲቲው አመራር ችግር ሲከሰት በወቅቱ አላወያየንም 6. የትምህርትና የፈተና ጊዜ ወደ መስከረም እንዳይተላለፍብን፤ በአስቸኳይ ተወስኖ ይገለጽልን፤

የሀይማኖት አባቶች ምክር አዘል መልዕክቶችን አስተላልፈዋል፡፡ ሀይማኖታዊ ስነምግባራትን ተማሪዎች መከተል እንዳለባቸው እና ሰብዓዊ ፍጡሮች እንደመሆናችን በአንድነት፣ በፍቅር፣ በመተሳሰብና በሰላም መማር እንደሚገባቸው እንዲሁም ወንድማማችነትን በማጠናከር ሀገራዊ አንደነትን መገንባት እንደሚገባ መክረዋል፡፡ 

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ እና የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዘይኑ ጀማል በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲዎች የአስተሳሰብ ልእልና የሀገር አንድነት የሚጎለብትባቸው፤ ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር የሚካሄድባቸው፤ የፈጠራ ስራዎች የሚስፋፉባቸው እንጂ የብጥብጥና የሁከት መነሻ ፈጽሞ ሊሆኑ እንደማይችሉ እና የህግ የማስከበሩ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አጽእኖት ሰጥተው ገልጸዋል፡፡

አቶ ንጉሱ ጥላሁን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ሃላፊ መድረኩን ሲያጠቃልሉ እንዳሉት የሀይማኖት አባቶች ይህ ጉዳይ አሳስቦአቸው ከሩቅም ከቅርብም ዩኒቨርሲቲው ሰላም እንዲሆን፣ ተማሪዎች እምነት እንዲያድርባቸው፣ ጥበቃ እንዲደረግላቸው የከተማው ህብረተሰብ ጭምር እንዳረጋገጠላቸው ተናግረዋል፡፡

ፍተሻ በተመለከተ ጠንከር ያለ ፍተሻ እየተደረገ ነው፡፡ መረጃች በበቂ ሁኔታ የሚሰጡ አግኝተናል፣ በፍተሻው ወቅት የጸጥታ አካሉ ሌት ተቀን እየሰራ እንደሆነ፤ሆኖም የጸጥታ አካሉ ለተማሪው ያለውን ከለላና ጥበቃ እንደላላ ዘመቻ ይደረግበታል እንጂ ስራውን በአግባቡ እየተወጣ ይገኛል፡፡ የተሳሳተ ካለ ደግሞ ተቋሙ ባለው አሰራር ይርማል ብለዋል፡፡

እኛ የመጣንው ህንጻው ሲቃጠል አይደለም፤ እዚሁ አብረናችሁ እያለን፣ አይናችን እያየ ነው የተቃጠለው፡፡ ከውጭ አይደለም ከውስጥ ነው፤ በስህተት አይደለም ሆን ተብሎ ታቅዶ ነው የተቃጠለው፡፡በምንም መስፈርት ህንጻ ያቃጠለ፣ የሰውን ልጅ በብሄሩ ፈርጆ በኮብል ካልገደልኩ የሚል የዩኒቨርሲቲው ህግ ቢተወውም፣የሀገሪቱ ህግ አይተወውም፤ ሴኔቱ ቢተወው እንኳን እራሱ ሴኔቱ ተጠያቂ ይሆናል ብለዋል፡፡
ተማሪው ምርጫው የራሱ ነው፡፡ በጋራ አንማርም አይሰራም፤ አልማርም ይሰራል፡፡ በጋራ አንመገብም አይሰራም፤ አልመገብም ይሰራል፡፡ ማንም በእኔ ጉረሮ አትበላም ሊለኝ አይችልም፤ እኔ አልባለም ካላልኩ፤ማንም በእኔ ቦታ ሆኖ አንማርም፣ አልበላም ሊል አይችልም፡፡

የግለሰቦች ውሳኔ ይከበራል፤ ግለሰቦች የወሰኑትን ውሳኔ አይፈጽሙም፣ አይወስኑም የሚል ይህንን አስገድጀ እፈጽማለሁ የሚል ጉልበተኛ አይኖርም፡፡
የትምህርት ጊዜውን በተመለከተ አመራሩ፣ መምህራንና ሴኔቱ መክሮ ትምህርት የሚጀመርበትን እና ፈተና የሚሰጥበትን ቀን በአስቸኳይ ወስኖ ያሳውቃል ብለዋል፡፡
ሴኔቱ በተጋነነ ሁኔታ፣ አላግባብ የአንድን ብሄር ተማሪ ብቻ ለይቶ ውሳኔ ሰጥቷል የተባለው ስህተት ነው፡፡ ሴኔቱ ቴክኒካል ስህተት ሰርቶ ከሆን ያርማል፡፡ አስተዳደራዊ ጥያቄዎች በዩኒቨርሲተው ይመለሳሉ ብለዋል፡፡
የተማሪውን ደህንነት ለመጠበቅ እንሰራለን፣እናንተም ተባበሩን፣ በብሄር ማሰብ ፣ በዘር ማሰብ የበታችነት ነው፤ትልቅ የምንሆነው ስለአንድነታችን፣ ስለወንድማማችነታች፣ ስለሀገራችን ስናስብ ነው፡፡ የሁሉም ብሄር መብት የሚከበረው የሌለውን መብት ስናከብር ነው ብለዋል፡፡
በመጨረሻም የእርቅና የሰላሙን ሁኔታ የሚከታተሉ ከሁለቱም ብሄሮች አምስት አምስት አባላት ያሉበት አካላት ተመርጠው፣ በስብሰባው ላይ የተገኙት አካላትን ጨምሮ በጋራ የእራት ፕሮግራም በማካሄድ በስኬት ተጠናቋል፡፡