Notice
የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ረ/ፕ ደረጀ አጅቤ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ካደረጉ በኋላ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች አገልግሎት የሚሰጡ ማህበራት ያስመዘገቧቸውን ስኬቶችና ያሉባቸውን ክፍተቶች የሚያሳይ የዳሰሳ ጥናት ተደርጓል ብለዋል፡፡ አክለውም ማህበራቱን ከሚያደራጁና ከሚደግፉ የመንግስት አካላት እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲው ምን ይጠበቃል በሚሉ ጉዳዮች ላይ ቀጣይነት ያለው የምክክር መድረክ እንደሚዘጋጅ ገልጸዋል፡፡
የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ስራዎች ለ3ኛ ወገን የሚሰጡት ልምድ፣ ስኬቶችና ተግዳሮቶች በሚል ርዕስ ጥናታዊ ፅሑፍ ያቀረቡት የዩኒቨርሲቲው እቅድ ዝግጅት፣ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል በፍቃዱ እንደገለጹት የጥናቱ ዋና አላማ ስራዎችን በ3ኛ ወገን ማሰራት ያስገኘውን ስኬት መለየትና እያጋጠሙ ላሉ ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት እንዲያግዝ ነው ብለዋል፡፡ ዳይሬክተሩ በጥናቱ ውስጥ በርካታ ስኬቶች መኖራቸውን አመላክተዋል፡፡ አያይዘውም የምግብ ጥራት ችግር፣ የስነ-ምግባር ችግር፣ የአቅም ውስንነት፣ በአቋራጭ የመበልጸግ ስሜት መኖር፣ የዋጋ ግሽበት መኖር፣ አደራጅ መ/ቤቱ ተገቢውን ድጋፍና ክትትል አለማድረግ፣ የአቅርቦት እጥረት መኖር፣ የአመለካከትና የጥገኝነት እንዲሁም ሌሎችም ተግዳሮቶች እንዳሉ በጥናቱ ተመላክቷል ብለዋል፡፡
በመድረኩም ላይ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በምግብ ዝግጅትና መስተንግዶ፣ በጽዳት፣ በጥበቃ፣ በተማሪዎች መዝናኛ ክበብ የተሰማሩ የማህበራት ተወካዮች፣ በየደረጃው ያሉ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ የዞንና የወረዳ ቴክኒክና ሙያ እንተርፕራይዝ ፅ/ቤት፣ የአደራጅ ፅ/ቤት ሀላፊዎች እና ሌሎችም የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈውበታል፡፡
ተሳታፊዎቹ ጥናቱን መሰረት አድርገው በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶችን አንስተው የጋራ ውይይት አድርገዋል፡፡ እንዲሁም ዩኒቨርሲቲው ስራዎችን ለ3ኛ ወገን በማስተላለፉ ያስገኛቸው ስኬቶችን አጠናክረው ማስቀጠል እንዳለባቸውም ጭምር ተነጋግረዋል፡፡ በከተማው ውስጥ እየተስፋፋ የመጣውን የስራ አጥነት ችግር እያንዳንዱ አካል በትኩረት ሊሰራበት ይገባል ተብሏል፡፡ ስራና ሰራተኛን የማገናኘት ተግባር ዩኒቨርሲቲው አጠናክሮ እንደሚቀጥልበት ተገልጿል፡፡
በመጨረሻም በጥናቱ የተገኙና ከተሳታፊው የተመላከቱ ችግሮችን እያንዳንዱ አካል በባለቤትነት ወስዶ እንዲሰራባቸው የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡