Notice

ዩኒቨርሲቲው ስነ ህይወታዊ የቡና ገለፈት ማስወገጃ ፕሮጀክት አሰመረቀ

News

በአካባቢ ብክለት፣ በጤና ላይ ከፍተኛ ችግር እንደነበረና የቡና ተረፈ ምርት ቆሻሻውን የማስወገድ ችግር መነሻ በማድረግ በሶስት ቀበሌዎች ለሶስት ዓመታት ያህል ስነ ህይወታዊ የቡና ገለፈት ማስወገጃ ፕሮጀክት በትሎች አማካኝነት የቡና ገለፈትን ወደ ተፈጥሮአዊ ማዳበሪያነት የመለወጥ ሂደት ምርምር ሲደርግ፣ ትሎችን የመለየት፣ የማባዛትና የተፈጥሮ ማዳበሪያ የማምረትና በቡና አምራች ገበሬዎች ማሳ ላይ ተሞክሮ ውጤታማነቱ ተረጋግጦ በመጠናቀቁ የእለቱ የክብር እንግዶች በተገኙበት ፕሮጀክቱ ተመርቆ ለ21 ስራ አጥ ወጣቶች ቴክኖሎጂውን የማስተላለፍ ስራ ተከናውኗል፡፡

በምርቃቱም ላይ የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲቱዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ካሳሁን ተስፋዬ፣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የኢኮኖሚ አማካሪ ሙሉጌታ ጋሼ፣ የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የጥናትና ምርምር ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር አልማዝ አፈራ እና የዞን አመራሮች ፕሮጀክቱን መርቀዋል፡፡ እንዲሁም የወረዳና የቀበሌ አመራሮች፣ የአካባቢው ነዋሪዎችና የሀገር ሽማግሌዎች፣ ተጠቃሚዎች፣ የዲላና የመቱ ዩኒቨርሲቲ ፕረዚዳንቶች እና ተመራማሪዎች በምረቃው ላይ እንደተገኙ ታውቋል፡፡

የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስና ቀመር ኮሌጅ ዲንና ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ገዛኽኝ ደግፌ እንዳሉት የፕሮጀክቱ አጀማመር በይርጋለም አካባቢ ብዙ የቡና አምራች ማህበራት በመኖራቸውና የቡና ገለፈቱ መርዛማ በመሆኑ በአካባቢ ብክለት ላይ ከፍተኛ ችግር እንደነበረው አስረድተዋል፡፡ ችግር ለመፍታት የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጅ ኢንስቲተዩት ተመራማሪዎችን ሲጋብዝ የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ፕሮፖዛል በማቅረብ በኢንስቲትዩቱ ድጋፍ በይርጋለም አካባቢ በ3 ቀበሌዎች ለምርምር የሚሆኑ ትሎችን በመለየት፣ በማባዛትና በመጠቀም የቡና ገለፈትን ወደ ተፈጥሮ ማዳበሪያነት በመቀየርና በአርሶ አደሮች ማሳ ላይ በመሞከር ውጤታማ በመሆኑ ለ21 ስራ አጥ ወጣቶች ስራ ዕድል በመፍጠር ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ተመራማሪው አክለውም ከማዳበሪያው ማምረት ባሻገር  የዶሮና የአሳ እርባታ በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አርሶ አደሮች በበኩላቸው ተሞክሮ ውጤታማ እንደሆነ ከኬሚካል ማዳበሪያው በጣም የተሻለ መሆኑን ገልፀው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው የቡና ምርት የማሳደጉ ሁኔታ ከፍተኛ መሆኑን እና ከአካባቢ ብክለት ነፃ እንደሆኑና እፎይታ እንዳገኙ ገልፁው የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎችን አመስግነዋል፡፡

በዕለቱም የፕሮጀክቱን ሰነድ ዶ/ር ገዛኸኝ ደግፌ ለሲዳማ ዞኑ መስተዳደር በኢት/ባ/ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አማካኝነት አስረክበዋል፡፡ የፕሮጀክቱ ሂደት ምን እንደሚመስል በዶ/ር ገዛኸኝ  ደግፌ ለተሳታፌዎቹ ቀርቦ ሰፊ ወይይት ተካሄዷል ፡፡

የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ካሳሁን ተስፋዬ በበኩላቸው ጽ/ቤታቸው ለጥቅም የቀረቡና ችግር ፈቺ ቴክኖሎጅዎችን ለማህበረሰቡ እንዲጠቀምባቸው ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡ በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ በሆኑት በዶ/ር ገዛኸኝ መሪነት ለተካሄደው ምርምር የመጀመሪያውን ዙር ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ አክለውም ዶ/ር ካሳሁን  የማይጠቀመውን የቡና ገለፈት በትሎች አማካይነት ወደ ተፈጥሮአዊ ማዳበሪያነት በመለወጥ ጥቅም ላይ የማዋል ፕሮጀክት የቡና ምርቱ ኦርጋኒክ እንዲሆን ምርምሩ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው አብስረዋል፡፡ ምርምሩ ለ3 አመታት ሲካሄድ ቆይቶ የቡና አምራች አርሶ አደሮችን ችግር ፈትቶ የቡና ምርታማነትን በማሳደጉና የአካባቢ ብክለት የሚያመጣውን ችግር በመወገዱ ለ21 ወጣቶች የስራ ዕድል በመፍጠሩና የማህበረሰቡን ችግሮችን በመፍታታቱ ኢንስቲትዩቱ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ ይህንን ፕሮጀክት በሌሎች ተረፈ ምረቶች ላይ የማስፋት ስራ እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡    

በመጨረሻም የደ/ብ/ዩ ጥናትና ምርምር ማህ/አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር አልማዝ አፈራ እንደተናገሩት የቡና ገለፈትን በትሎች አማካኝነት ወደ ተፈጥሯዊ ማዳበሪያነት በመቀየር፣ ምርታማነትን በማሳደግ፣ የስራ ዕድል በመፍጠር ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ከፍተኛ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ አያይዘውም በማሳቸው ላይ በምርምር የተገኘውን የተፈጥሮ ማዳበሪያ ቴክኖሎጂ የተጠቀሙ  የቡና አምራች አርሶ አደሮች ውጤታማ መሆናቸውን አስረድተው በዩኒቨርሲቲው የተገኘውን ቴክኖሎጂ ለቡና አምራች ማህበረሰብ የማስፋት ስራ መሰራት እንዳለበት አሳስበው ለዚህ ምርምር ለተባበሩ ሁሉ ምስጋና አቅረበዋል፡፡