Notice
ከተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የጸጥታ አካላት፣ የመንግስት ተወካዮች እና የተማሪዎች ህብረት አባላት ጋር ከታህሳስ 13-15/2012 ዓ.ም ድረስ ሰፊ ውይይት ተካሄደ፡፡
ውይይቱን የመሩት ከፌደራል መንግስት ተወክለው የመጡት አቶ ዳዊት የሽጥላ ከብልጽግና ፓርቲ፣የተከበሩ አቶ አንድነት ሰብስቤ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣አቶ ከበደ ግዛው ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አቶ አህመድ መሀመድ ከኦሮሚያ ክልል መንግስት አመራር ናቸው፡፡የውይይቱ አላማ የዩኒቨርሲቲውና የአካባቢው ማህበረሰብ ስለ ዩኒቨርሲቲው ያለው አረዳድ ምን እንደሚመስል ለማወቅ፣ የሚፈጠሩ የጸጥታ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት፣ መወሰድ ያለባቸውን የመፍትሔ ሀሳቦችን ለማንሳት፣ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ እንዲሁም ተማሪዎቹ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ተረጋግተው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ለማስቻል የተዘጋጀ የምክክር መድረክ መሆኑን ተገልጿል፡፡
በተማሪዎች፣በመምህራን፣በአስተዳደር ሰራተኞች በአካባቢው ማህበረሰብ ከተነሱት ዋና ዋና ችግሮች መካካል ውጫዊ ፖለቲካው የሚያሳድርበት ጫና፣ከኦሮሚያ ዩኒቨርሲቲ ተፈናቅለው የመጡ ተማሪዎች ጉዳይ፣በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ብሄር ተኮር ጥቃት እየደረሰባቸው የሚገደሉ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጉዳይ፣የመንግስት ህግ ማስከበር አለመቻል፣ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው ውስጣዊ ችግሮች ለምሳሌ ያህል አልፎ አልፎ የሚከሰቱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች፣ የበር ጥበቃ ፍተሻ መላላት፣የተማሪዎች የምግብ ሜኑ ገንዘብ ዝቅተኛ መሆን፣በአካባቢው የሚስተዋለው የመጥፎ ሱስ አምጭ ንግዶች መስፋፋት፣የሁለተኛው በር መዘጋት፣የመግቢያና መውጫ ሰዓት ጉዳይ፣የውጭ መብራትና መንገድ ችግር የሚሉት ይገኙበታል፡፡
በተጨማሪም ደብረብርሃንና አካባቢው ሰላማዊ እንቅስቃሴዎች የሚስተዋሉበት፣ ብሔር ብሔረሰቦች በሰላምና በፍቅር አብረው የሚኖሩባት፣ እንግዳ ተቀባይና ጨዋ ህዝብ ያለው አካባቢ እንደሆነ ተሳታፊዎቹ ተናግረዋል፡፡ ዜጎች በብሔራቸው፣ በቋንቋቸው እና በሚከተሉት እምነት እንዲሁም በሚያራምዱት ርዕዮተ አለም ምክንያት አድሎና መገለል ሊደርስባቸው አይገባም ተብሏል፡፡ መንግስት የህዝቦችን ሰላም ለማረጋገጥ የህግ በላይነትን ማስከበር ይጠበቅበታል ሲሉ ተሳታፊዎቹ ገልጸዋል፡፡
ለተነሱት ችግሮች የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንትና የኮሚቴው አባላት ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ንጉስ ታደሰ(ዶ/ር) እንደገለጹት የዩኒቨርሲቲው መኖር ለአካባቢው ማህበረሰብ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል፡፡ ህብረተሰቡም ያለውን ፋይዳ በአግባቡ ተገንዝቦና ተረድቶ እንዲጠብቀው ጥሪ አቅርበዋል፡፡እንደ ፕሬዚዳንቱ የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ከሞላ ጎደል ትምህርት ሳይቋረጥ እየሰጠ ያለው አብዛኛው ተማሪ፣መምህርና የአስተዳደር ሰራተኞች ሰላም ፈላጊዎች በመሆናቸውና የአካባቢው ማህበረሰብም ሰላም ወዳድ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የሚፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች ውስጣዊ መንስኤዎች ብቻ ሳይሆን ውጫዊ መንስኤዎችም አባባሽ እንደነበሩ ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡በአሁኑ ሰዓት ዩኒቨርሲቲዎች ከተልዕኮዎቻቸው ወጥተው የጸጥታ ስራ ላይ ተሰማርተዋል ያሉት ፕሬዚዳንቱ የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ መምህራንና አስተዳደር ሰራተኞች ለዩኒቨርሲቲው ደህንነት በማሰብ በሁለት ሽፍት ጥበቃ እያካሄዱ በመሆናቸው ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል ብለዋል፡፡ሁለተኛው በርና የመውጫ ሰዓት ገደብ የተደረገውም ለተማሪዎች ደህንነት ሲባል እንጅ ተማሪዎችን ለመጉዳት ታስቦ እንዳልሆነ ግንዛቤ መወሰድ አለበት ብለዋል፡፡
ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የተወከሉ አቶ ከበደ ግዛው እንዳሉት በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች በተከሰተው ችግር አማካኝነት በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲም ተመሳሳይ ችግሮችን ለማስነሳት ከውጪ ተልዕኮ ተቀብለው ጉዳት ለማድረስ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩ አካላት እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡ ሆኖም ግን የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች፣ መምህራን፣ አስተዳደር ሰራተኖች እና የተማሪዎች አደረጃጀት በሰሩት የተቀናጀ ስራ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የከፋ ችግር ሳይከሰት ማቆየት ተችሏል ብለዋል፡፡
ከህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የተወከሉ ክቡር አቶ አንድነት ሰብስቤ በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥና የሚታዩ ችግሮችን ለይቶ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ የኮሚቴው ዋነኛ ተልዕኮ ነው ብለዋል፡፡ በየቦታው ተፈናቅለው የሚገኙ ተማሪዎችን ወደ ተመደቡባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ገብተው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል ብለዋል፡፡
አቶ ዳዊት የሽጥላ ከብልፅግና ፓርቲ እንዳሉት የኮሚቴው ተልዕኮ በሁለቱ ትላልቅ ክልሎች በተለያየ ጊዜ በሚከሰቱ ግጭቶች ሰላማዊ መማር ማስተማሩ እየተስተጓጎለ ስለሆነ በሁሉም የሀገሪቷ ዩኒቨርሲቲዎች ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን፣ የአመቱ መማር ማስተማር ሳይስተጓጎል እንዲቀጥል፣ የህግ የበላይነት እንዲከበር ለማስቻልና ሁሉን አቀፍ መፍትሄ ለማስቀመጥ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ተቋማቱ በሚገጥማቸው ችግሮች ላይ ተመካክረን መፍትሄ ለመስጠት እንደሆነና ማስተካከያ ሰጥተን ለመሄድ ነው ብለዋል፡፡ከዚሁ ጋር ተያይዞ መንግስት የችግሩን ምንጭና ባለቤቶችን መለየትና ርምጃ መውሰድ የሚያስችል ስራ እየተሰራ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡የተፈናቀሉ ተማሪዎችን በተመለከተ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት እየተሰራም ነው ብለዋል፡፡