Notice

የኢንዱስትሪዎች መምጣት ፀጋ እንጂ እዳ መሆን የለበትም ተባለ

News

በዩኒቨርሲቲውና በኢንዱስትሪው መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ አጠናክሮ በጋራ መስራትና የተሻለ ውጤት ማምጣት ከውይይቱ የሚጠበቅ ተግባር ነው ብለዋል፡፡ በደብረብርሃንና አካባቢው በርካታ ኢንዱስትሪዎች መምጣታቸውን መንግስት ታሳቢ አድርጎ ዩኒቨርሲቲው ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ አፕላይድ ዩኒቨርሲቲ እንዲሆን አቅጣጫ ተቀምጧል ብለዋል፡፡ ተማሪዎች በኢንዱስትሪው ውስጥ በቂ የተግባር ልምምድ እንዲያደርጉ ያስችላል ሲሉ ተናግረዋል፡፡


ለኢንዱስትሪው የሚያስፈልጉ ቴክኖሎጂዎችን የማሻሻል፣ የመፍጠርና የማሳደግ ስራን አጠናክሮ በመስራት ዩኒቨርሲቲውና ኢንዱስትሪው በጋራ ተሳስረው የመሀል አገሩን አጠቃላይ የሰው ሀይል ፍላጎት ማሟላት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡ የኢንዱስትሪዎች መምጣት ለአካባቢው ህብረተሰብ ፀጋ እንጂ እዳ እንዳይሆኑ በበላይነት የሚመራው የዞኑ ኢንቨስትመንት ቢሮ ሀላፊነቱን በሚገባ ሊወጣ ይገባል ሲሉ ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው ኢንዱስትሪ ትስስር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በሆኑት ረ/ፕ ሰለሞን መንግስቴ የኢንዱስትሪ ትስስር ፅንስ ሀሳብና ጠቀሜታው የሚል የመነሻ ጹሑፍ ቀርቧል፡፡ እንዱስትሪዎችና ዩኒቨርሲቲው በሚፈጥሩት የጋራ ትስስር ያሉ መልካም ዕድሎች፣ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች እና የሚያስገኙትን ጥቅም በዝርዝር በመነሻ ጹሑፍ ውስጥ ለማሳየት ሞክረዋል፡፡ በጋራ ምርምር ማድረግ፣ ስልጠና መስጠት፣ ማማከር፣ አዳዲስ በሚከፈቱ የትምህርት ካሪኩለም ላይ ተሳትፎ በማድረግ፣ ለተማሪዎች የተግባር ልምምድ በመስጠት፣ ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን የሰው ሀይል ለማሟላት ወሳኝ የትምህርት ዓይነቶች በመቅረፅ እና የጋራ ቤተ-ሙከራ በማቋቋም ዩኒቨርሲቲውና ኢንዱስትሪዎቹ በቅንጅት መስራት እንደሚችሉ አመላክተዋል፡፡ ሌላኛው አቅራቢ አቶ ጌታቸው ንጋቱ የክልል አካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ ባለስልጣን ተወካይ በደብረ ብርሃንና አካባቢው ያሉ ፋብሪካዎች የቆሻሻ አወጋገድና በህብረተሰቡ ላይ ያስከተሉትን ተዕፅኖ የዳሰሰ ጥናታዊ ጹሑፍ አቅርበዋል፡፡

በሀገራችን ከኢንዱስትሪ መስፋፋት ጋር ተያይዞ የአካባቢ ብክለት ለመከላከል አዋጅ ቁጥር 299/1995 በፌደራል ደረጃ እና 181/2003 በከልል ደረጃ ወጥተው ስራ ላይ መዋላቸውን ተገልጿል፡፡ እነዚህ አዋጆች ኢንዱስትሪው ዘላቂ በሆነ መንገድ ከአካባቢውና ከማህበረሰቡ ጋር ተጣጥሞ እንዲሄድ የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ የፋብሪካ ባለቤቶች ህጉን ተግባራዊ እያደረጉት እንዳልሆነ አቶ ጌታቸው ተናግረዋል፡፡ በመቀጠልም በቀረቡት ሁለት የመነሻ ፁሑፎች ላይ በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ከተሳታፊዎቹ በኩል ተነስተው ከመድረኩ ማብራሪያና ምላሽ እንደተሰጠባቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡

በመጨረሻም የደ/ብ/ዩ የጥናትና ምርምር ማህ/አገ/ም/ፕሬዚዳንት አልማዝ አፈራ (ዶ/ር) የማጠቃለያ ሀሳብ ሰጥተዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ኢንዱስትሪ ትስስር ዳይሬክቶሬት ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ መልካም የሚባሉ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡ አክለውም ምንም እንኳን ስራው በሚጠበቅበት ደረጃ ያደገ ባይሆንም ጅምሮቹ አበረታችና ተስፋ ሰጪ ናቸው ብለዋል፡፡ ፋብሪካዎች በራቸውን ክፍት አድርገው በጋራ ለመስራት ፍቃደኛ ያለመሆን አዝማሚያዎች ይስተዋላሉ ብለዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው መምህራንና ተመራማሪዎች እውቀታቸውን የሚያበለፅጉበት እና የኢንዱስትሪዎችም ችግር በምርምር እንዲፈቱ ተቀራርበን መስራት ይጠበቅብናል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡