Notice

ደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ለጤና ባለሙያዎች ስልጠና ሰጠ

News

የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ክሊኒክ ሀላፊ የሆኑት አቶ ሸንቁጥ አራጋው እንዳሉት በዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ክሊኒክ ለሚሰሩ የፋርማሲ፣ የክሊኒካልና የላብራቶሪ ባለሙያዎች እና ካርድ ክፍል ለሚሰሩ ሰራተኞች ስልጠናው እንደተሰጠ ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በሰ/ሸዋ ዞንና አካባቢው በኮቪድ-19 ቫይረስ ተጠቂ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በለይቶ
ማቆያ ማዕከልነት እንዲያገለግል ተወስኖ በርካታ ዝግጅቶች ሲደረግ የቆየ መሆኑን ገልጸው የጤና ባለሙያዎችን በክህሎትና በስነ-ልቦና አንፆ ማዘጋጀት ተገቢ ተግባር ነው ብለዋል፡፡ ቀደም ሲል በፅዳት፣ በጥበቃና በምግብ ዝግጅት የስራ መስክ ላይ ለተሰማሩ ሰራተኞች በኮቪድ-19 ወረርሽኝን ዙሪያ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጥቷል ነው ያሉት፡፡

በደ/ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ህክምና ኮሌጅ መምህር የሆኑት አብርሃም ሽታው እንደገለጹት በኮቪድ-19 ቫይረስ ተጠርጥረው በለይቶ ማቆያ ውስጥ የሚገቡ ሰዎችን እርዳታ ለሚሰጡ የጤና ባለሙያዎች የተዘጋጀ ስልጠና ነው ብለዋል፡፡ ነርሶች፣ የፋርማሲና የላብራቶሪ ባለሙያዎች ስራቸውን በሚሰሩበት ወቅት ራሳቸውን ከኢንፊክሽን መከላከል የሚያስችላቸውን ስልቶች እንዲሁም ታካሚውን የሚረዱበትን መንገድ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ስልጠና እንደነበር ተናግረዋል፡፡ እንደ መ/ር አብርሃም ገለፃ ህብረተሰቡ ከጤና ባለሙያዎች የሚሰጡ ምክሮችን እና መንግስት ያወጣቸውን አዋጆችን ተግባራዊ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል፡፡

በስልጠናው ተሳታፊ የሆኑት በዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ክሊኒክ ውስጥ የጤና መኮንን ባለሙያ ወ/ሮ ዘነበወርቅ ጌታቸው እና አቶ ነጋ አያሌው እንዳሉት በለይቶ ማቆያ ውስጥ በኮቪድ-19 ቫይረስ ተጠርጥረው ለሚገቡ ሰዎች ሊደረግላቸው የሚገቡ ህክምናዎችንና እርዳታዎችን እንዲሁም ራሳቸውን ከኢንፊክሽን መከላከል የሚያስችላቸውን ክህሎት እንዳገኙ ተናግረዋል፡፡ አክለውም እያንዳንዱ ባለሙያ ስራውን በጥሩ ሁኔታ እንዲያከናውን በቂ እውቀትና የስነ-ልቦና ዝግጅት እንዲኖረው የሚያግዝ ስልጠና መሆኑን ገልጸዋል፡፡