Notice

ደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ያሰለጠናቸውን የድህረምረቃ ተማሪዎች አስመረቀ

News

የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደረጀ አንዳርጌ ያለንበት ወቅት ከኮረና ቫይረስ ጋር በተያያዘ የመማር ማስተማር  ሰርዓቱን አስቸጋሪ እንዳደረገው ተናግረዋል፡፡የባከኑ ትምህርቶችን በዕቅድ ይዘን  የሳይንስና ከፍተኛ ትም/ሚኒስቴር በሰጠው አቅጣጫ መሰረት የዲጅታል ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ተማሪዎች ባሉበት ሆነው የቀሯቸውን ኮርሶች እንዲያጠናቅቁና የድህረ ምረቃ ጽሁፋቸውንም እንዲያቀርቡ ተደርጓል ብለዋል፡፡ የዛሬው የምረቃ ስነስርአትም ከዚህ በፊት ሲደረግ እንደነበረው ተሰባስቦ  የሚካሄድ አይደለም ነው ያሉት፡፡

በልዩ ልዩ ምክንያት ለምረቃ መረጃቸውን ያላሟሉ ተማሪዎችን ጨምሮ ወደፊት የበሽታው ስርጭት ሲቀንስ የጤና ተመራቂ ተማሪዎችን ቃለ-መኃላ በማስገባት የተለመደውን ሙሉ የምረቃ ስነ ስርዓት የምናከናውን ይሆናል ሲሉ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ በመጨረሻም ለተመራቂ ተማራዎቹ  በተመረቁበት ሙያ የዜግነት ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ በማሳሰብ እንኳን ደስ አላችሁ ሲሉ  ደስታቸውን ገልጸዋል፡፡

የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች   ሪከርድ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር በቀለ መአዛ የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ሴኔት በወሰነው ውሳኔ መሰረት በዛሬው ዕለት  የሚፈለግባቸውን አሟልተው ያጠናቀቁ  የድህረ ምረቃ ተማሪዎች ከ7 ከሌጆች  በ21 የትምህርት መሰኮች የሰለጠኑ  ወንድ 209 ሴት 52 በድምሩ 261 ተማሪዎች ብቻ በሁለተኛ ድግሪ ተመርቀዋል ብለዋል፡፡

የአካውንቲግና ፋይናንስ ዲፖርትመንት ተማሪና 3.91 ከፍተኛ ነጥብ በማምጣት ተመራቂ የሆነው ገብረሃና ደበበ የኮረና ቫይረስ በተከሰተበት በዚህ ወቅት ተምሮና ከፍተኛ ነጥብ አምጥቶ መመረቅ መቻል እድለኝነትም ጭምር ነው ያለ ሲሆን እንደተማረ ሰው በስለጠንኩበት ሙያ ሀገሬን ለማገልገል ዝግጁ ነኝ ብሏል፡፡