Notice

የበረሀ አንበጣ በአርሶ አደሩ ሰብል ላይ እያደረሰ ያለውን ውድመት ለመከላከል የደረሱ ሰብሎችን የማንሳት ዘመቻ ተካሄደ

News

ዘመቻው ጥቅምት 03/2013 ዓ.ም የተካሄደ ሲሆን የበረሀ አንበጣው በደረሱ ሰብሎች ላይ ተጨማሪ ጉዳት እንዳያስከትልም ከ350 በላይ በጎ ፍቃደኞች በዩኒቨርሲቲው በተዘጋጀላቸው ሰባት የህዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች ወደ ቀወት ወረዳ በመጓዝ ነው ሰብል የማንሳት ተግባር ያከናወኑት፡፡

የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የመረጃ አስተዳደርና ትንተና ስርአት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና የዘመቻው ግብረ ኃይል አስተባባሪ ታምራት ቸሩ (ዶ/ር) የበረሀ አንበጣ መንጋው በክልላችን በሰሜን ሸዋ ዞን በተወሰኑ ወረዳዎች እየተስፋፋ በመምጣቱ በአርሶ አደሩ ሰብል ላይ ከፍተኛ ውድመት እያደረሰ ይገኛል ብለዋል፡፡ ጉዳቱ ከዞንና ከክልል አልፎም የሀገር ስጋት እየሆነ በመምጣቱና በአርሶ አደሩ ብቻ ችግሩ የሚቀረፍ ባለመሆኑ የሁሉንም አካላት እርብርብን የሚፈልግ ነው ብለው ከዩኒቨርሲቲው ኮሚኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ጋር በተደረጋ የጋራ የማስተባበር ስራ እንደ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዙር የበጎ ፍቃድ ዘመቻ አዘጋጅተን በሰሜን ሸዋ ዞን ቀወት ወረዳ ጉዞ ለማድረግ ችለናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አርሶ አደሩ የደረሱ ሰብሎችን መሰብሰብ በሚጀምርበት ወቅት ሰብሉ በአንበጣ መንጋ እየወደመበት ይገኛልም ነው ያሉት፡፡
የአርሶ አደሩን ህይወት መታደግ ማለት የራስን ህይወት መታደግ ማለት ነው ያሉት አስተባባሪው የአርሶ አደሩ ህይወት አደጋ ላይ ነው ማለት የከተማው ነዋሪም የመኖር ህልውናው አደጋ ላይ እንደሆነ መረዳት ተገቢ ነው፡፡ የደረሱ ሰብሎችን የማንሳት ዘመቻው የደብረብርሃን ከተማ ወጣቶችንም በማሳተፍ የተካሄደና በአጭር ጊዜ የታቀደ ቢሆንም ውጤታማ እንደነበርና በአንድ ጊዜ ብቻ የሚያበቃም እንዳልሆነ ታምራት ቸሩ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የጥናትና ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት አልማዝ አፈራ (ዶ/ር) ለሚከሰቱ ማህበረሰባዊ ቀውሶች ዩኒቨርሲቲዎች በእውቀታቸው ማህበረሰቡን ከችግርና ከድህነት ማላቀቅ አንዱ ተግባራቸው ነው ብለዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓትም የበረሀ አንበጣ መንጋ በአርሶ አደሩ ሰብል ላይ እያደረሰ ያለውን ውድመት ለመከላከል ከሚወሰደው ጊዜያዊ የመፍትሄ እርምጃ በተጨማሪ ወደፊት በዘላቂነት በጥናትና ምርምር ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ አርሶ አደሩ ያጋጠመው የአሁኑ ችግር ለዩኒቨርሲቲዎች መነሻ እንደሚሆናቸውና የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲም የቤት ስራው አድርጎ እንደሚሰራበት ተናግረዋል፡፡
የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ መሰረት ሀይሌ በበኩላቸው የበረሀ አንበጣ መንጋ በሰሜን ሸዋ ዞን ቀወት ወረዳ ከመስከረም 24/2013 ጀምሮ መታየቱንና በዞኑ አቅም የመከላከል ስራ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረው መንጋው በአርሶ አደሩ ሰብል ላይ እያደረሰ ያለውን ውድመት ለመቀነስና ለማጠፋት በአርሶ አደሩ አቅም የሚቻል ባለመሆኑ በመንግስት በኩል ኬሚካል የመርጨትና ማህበረሰቡን በማደራጀትም የደረሱ ሰብሎችን ከማሳ ላይ ለማንሳት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ኃላፊዋ አያይዘውም አሁን ባለበት ሁኔታ በ9 ወረዳዎች 24 ቀበሌዎችን የሸፈነው የአንበጣ መንጋ 11 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ጉዳት በማድረሱ 76 በመቶ በሰብል ላይ ውድመት አድርሷል ብለዋል፡፡ በአሁን ሰዓት ሰብላቸው እየተነሳላቸው የሚገኙት አርሶ አደሮች ግማሽ መሬታቸው የሚሆነው በአንበጣ መንጋው የወደመባቸው መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
ከባለሃብቶች ጀምሮ ሁሉም የዞኑ ተቋማትና አጎራባች ወረዳዎች ጭምር ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙ የገለጹት ኃላፊዋ ከተባበርን አርሶ አደሮቻችንን መታደግ እንችላለን ነው ያሉት፡፡ በቀወት ፣ በሸዋሮቢት፣ በአጣዬ፣ በረኸት ወረዳዎች ላይ መረባረብ ማለት እንደ ሀገር የተጋረጠብንን አደጋ መመከት መሆኑን ተገንዝበን ዳር ቆሞ ከመተቸት ከመንግስት ጎን በመሆን አርሶ አደሩን እናግዝ ሲሉ ጥሪ ያቀረቡት ኃላፊዋ የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ከዞኑ ግብርና መምሪያ ጎን ሆኖ ሰራተኛውን በማሰለፍ ቦታው ድረስ ሄዶ ለሰራው ስራ ዝቅ ብዬ ምስጋና ላቀርብ እወዳለሁ ሲሉ ወ/ሮ መሰረት ኃይሌ ተናግረዋል፡፡
በሰብል የማንሳት ዘመቻው ተሳታፊ የነበሩትና በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ሙያዎች በማገልገል ላይ የሚገኙት አቶ ፈለቀ አሰፋ እና አቶ አበረ ወንድሙ የበረሃ አንበጣ መንጋው በአርሶ አደሩ ሰብል ላይ እያደረሰ ያለውን ከፍተኛ ውድመት በቶሎ ማክሸፍ ካልተቻለ እንደ ሀገር በሚኖረው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ማሳደሩ የማይቀር ነው ብለዋል፡፡ የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲም እንደዚህ አይነት ፕሮግራም አዘጋጀቶ አርሶ አደሩን ለመደገፍ እያደረገ ላለው ጥረት አድናቆታቸውን ገልጸው ሁሉም አካል ርብርብ በማድረግ እንደ ሀገር የተጋረጠውን አደጋ መመከት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንት ደረጀ አንዳርጌ (ዶ/ር) በበኩላቸው በመዝጊያ ንግግራቸው የበረሃ አንበጣ በህዝባችን ላይ እያደረሰ ያለውን ውድመት የመከላከል ስራ የዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ስራ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ዜጋ የውዴታ ግዴታ በመሆኑ እርብርብ ሊያደርግ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የቀወት ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኤሊያስ በፕሮግራሙ መዝጊያ ንግግራቸው በቀወት ወረዳ በተከሰተው የበረሃ አንበጣ መንጋ በአርሶ አደሩ መሬት ላይ እየደረሰ ያለውን የሰብል ውድመት ተገንዝባችሁና የችግሩ ህመም ተሰምቷችሁ ከደብረብርሃን ድረስ ተጉዛችሁ አቧራውን፣ ጸሃዩንና ድካሙን ችላችሁ ዋጋ ለከፈላችሁ የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ አመራር አካላት፣ ሰራተኞችና መምህራን ሁላችሁም በወረዳው መንግስትና ህዝብ ስም ልትመሰገኑ ይገባል ብለዋል፡፡
በቀወት ወረዳ ራሳ ቀበሌ ልዩ ስሙ ሰፊ በረት ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር የሺ ዳኝ ጎሽሜ ሁለት ቀላድ ተኩል መሬት ማሽላ በአንበጣ መንጋው ወድሞብኛል ብለዋል፡፡ የሌሎች የአምሰት አርሶ አደሮች ያገዳ ሰብል ጎን ለጎን አብሮ ወድሟል ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡
አርሶ አደር ሉሉ ሙልነህ በበኩላቸው ጤፍና ማሽላ እንደወደመባቸው የተናገሩ ሲሆን ሰፊ በረት፣ ቡራይ በረትና ጠዲቻ ተብለው በሚጠሩ ሶስት ጎረቤታማች ቀበሌዎች አርሶ አደሩ በሰብሉ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል ብለዋል፡፡