Notice

የአፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲዎች በ2014 በጀት ዓመት ዕቅዶቻቸው ላይ ግምገማዊ ስልጠና ማካሄድ ጀመሩ

News

 የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ንጉስ ታደሰ (ዶ/ር) ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የአፕላይድ ዩኒቨርሲቲዎች የ2014 እቅድ ግምገማዊ ስልጠና መድረክ በመካከላችን ስርዓት ያለው ትስስርንና ግንኙነታችንን ለማጠናከር፤ልምድና ተሞክሮ ለማግኘት ሀገር በቀል እውቀትና ዘመኑን የዋጀ የፈጠራና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም የህብረተሰባችንን እና የሀገራችንን ችግሮች ለመፍታት ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡

የኢንዱስትሪውና የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች በኢኮኖሚው ላይ ያላቸው ድርሻ እየጨመረ ሲሄድ መካከለኛና ከፍተኛ ክህሎት ያለው የሰው ሃይል እንዲኖር ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ስልጠናውን ከኢንዱስትሪዎች ጋር ትስስር በመፍጠር ብቁና ጥራት ያለው የሰው ሃይል ማፍራት ላይ የአፕላይድ ዩኒቨርስቲዎች ድርሻ ከፍተኛ እንደሚሆን ተናግረዋል ፡፡
ፕሬዚዳንቱ አያይዘውም አገራዊ የልማት ዕቅዶቻችን እንዲሳኩ የሳይንስ የቴክኖሎጂ የፈጠራ እና የሰው ሃብት ልማት ስራዎቻችንን ማጠናከር የሁላችንም ከፍተኛ ተቋማት ሃላፊነት ነው ሲሉም ነው የገለፁት፡፡
በመጨረሻም የዛሬው የ2014 ዓ.ም የአንድ አመት እቅድ ግምገማ ውይይት ከሁሉም አፕላይድ ዩኒቨርሲቲዎች በጋራ የምንሰራበትና ግንኙነታችንን መሰረት የምንጥልበት፤የተሻለ ግብዓት የምናገኝበት፡ እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
 
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ዴኤታ ሳሙኤል ክፍሌ(ዶ/ር) እንደተናገሩት ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ትምህርትና ስልጠና ሴክተሩ ሪፎርም መደረግ በመጀመሩ የአፕላይድ ዩኒቨርሲቲዎች ለሀገር እድገት የሚኖራቸው አስተዋፅኦ እንዲጨምር ከኢንዱስትሪዎች ጋር ያላቸው ትስስር ወሳኝነት አለው ብለዋል፡፡
ሚኒስቴር ዴኤታው አያይዘውም ዩኒቨርሲቲዎችንና እና ኢንዱስትሪዎችን የጋራ ፍላጎቶች ሊኖራቸው እና ሊናበቡ ይገባል ብለው ዩኒቨርሲቲዎቻችን ብቁ የሰው ሀይል እና ቴክኖሎጂ ለኢንዱስትሪው በማቅረብ ኢንዱስትሪዎቹ በአለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሚሆኑበትን ምቹ እድል እንዲፈጥሩ የሳይንስና ከፍተኛ ሚኒስቴር ይህንን የትብብርና የትስስር ስራ እየሰራ ይገኛል ሲሉም ነው ሚኒስቴር ዴኤታው ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ የገለፁት፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መ/ር እና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው ባስተላለፉት ቁልፍ መልዕክት አፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲዎች ሚና ምን መሆን እንዳለበት ገልፀው በዋናነት የቴክኖሎጂ ሽግግር እና የሰው ሀይል ልማት ላይ ማተኮር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ፕሮፌሰሩ አክለውም አሁን ባለው ሁኔታ የዩኒቨርሲቲዎች ቁጥር አሁን ካለው የህዝብ ብዛት አንፃር በቂ አለመሆኑን ተናግረው ጥራት ላይ በማተኮር በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን የሰው ሀይል ልማታችን ከፍተኛ መሆን አለበት ብለዋል፡፡
በሚኖረው የሁለት ቀናት ቆይታም የ2014 ዓ.ም እቅዶቻቸውን 15ቱም የአፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲዎች በተከታታይ እንደሚያቀረቡም ታውቋል፡፡